ሮሜ 12:1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ሰውነታችሁን ሕያው መሥዋዕት፥ ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም መንፈሳዊ አገልግሎታችሁ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ፥ ሕያውና የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጋችሁ ሁለንተናችሁን እንድታቀርቡ በመሐሪው በእግዚአብሔር ስም እለምናችኋለሁ፤ ይህም ማቅረብ የሚገባችሁ ቅንነት ያለው እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልግሎት ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ወንድሞቻችን፥ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። |
ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ።
ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር የከበረውንም ዘይት ታመጡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም፥ ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም።
መልካም፥ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
በእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው፥ ይህም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው።
የሰውነታችሁን ክፍሎች የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
እራሳችሁን የመታዘዝ ባርያዎች አድርጋችሁ ለምታቀርቡለት፥ ለምትታዘዙት ለእርሱ ሞትን ለሚያመጣው ለኃጢአት ወይም ጽድቅን ለሚያመጣው ለመታዘዝ ባርያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?
ከሥጋችሁ ደካማነት የተነሣ እንደ ሰው አነጋገር እናገራለሁ። የሰውነታችሁን ክፍሎች ሕገ ወጥነትን ለሚያመጣ ለርኩሰትና ለሕገ ወጥነት ባርያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ ስለዚህ አሁን የሰውነታችሁን ክፍሎች ቅድስና ለሚያመጣ ለጽድቅ ባርያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ።
ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ሁላችሁ ተስማምታችሁ በአንድ ልቡና እና በአንድ አቋም በአንድነት የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።
ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን።
ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለጌታ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንድትሆንለት ጌታ በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ አንተን መርጦሃል።
ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በምንም ዓይነት ነገር አላፍርም፤ ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ እንደ ወትሮው እንዲሁ አሁንም በሥጋዬ ይከብራል ብዬ በሙሉ ድፍረት እናገራለሁ።
ነገር ግን በእምነታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስስ ደስ ይለኛል፤ ከእናንተም ከሁላችሁ ጋር አብሬ ሐሤት አደርጋለሁ፤
ነገር ግን የሚያስፈልገኝን ሁሉ ተቀብያለሁ፤ ተትረፍርፎልኛልም፤ መዓዛው ያማረ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከኤጳፍሮዲጡስ ተቀብዬ በሁሉ ተሟልቶልኛል።
እንግዲህ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መመላለስ እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ ተቀብላችኋል፤ በእርግጥም እየተመላለሳችሁ ነው፤ ከዚህም በበለጠ አብዝታችሁ እንድታደርጉት በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን፤ እንመክራችኋለንም።
ማንም መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተሰቦቻቸው የሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መፈጸምን ይማሩ፥ ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኝ ነውና።
ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ቅጣት ስትቀበሉ ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል።
እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለማቅረብ፥ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ፥ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።