ሐዋርያት ሥራ 3:25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ፤’ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ የገባው ኪዳን ወራሾች ናችሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንተ የነቢያት ወራሾች ናችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ’ ብሎ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በሠራው ሥርዐትም የተወለዳችሁ ናችሁ፤ ለአብርሃም፦ ‘በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎታልና። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም፦ ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። |
እግዚአብሔርም አለ፦ “በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፥ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘለዓለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ።
አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፥ እርሱ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንደምትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንደሚጠፋ በእርግጥ እወቅ።”
ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፥ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ።
ልቡም በፊትህ ታማኝ ሆኖ አገኘኸው፥ የከነዓናዊውን፥ የኬጢያዊው፥ የአሞራዊውን፥ የፌርዛዊውን፥ የኢያቡሳዊውንና የጌርጌሳዊውን ምድር ለዘሩ ልትሰጥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፥ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ።”
የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር። ለብዙዎች እንደሆነ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደሆነ “ለዘርህም” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው።
መጽሐፍም፥ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፥ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤” ብሎ አስቀድሞ ለአብርሃም ወንጌልን ሰበከለት።
በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ለማብሰር ዘላለማዊውን ወንጌል የያዘ ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ፥ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ፤” እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።
ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሰዎች ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤