ኤርምያስ 26:13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታዘዙ። እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ለማምጣት የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የጌታን ድምፅ ስሙ፤ ጌታም በእናንተ ላይ የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አሁንም የአኗኗራችሁንና የሥራችሁን ሁኔታ ለውጣችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይኖርባችኋል፤ ይህን ብታደርጉ በእናንተ ላይ ሊያመጣ ያቀደውን ጥፋት ይመልሰዋል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፤ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። |
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
ይህም ትእዛዝ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር፣ ከብረት ማቅለጫው ምድጃ ባወጣኋቸው ጊዜ ድምፄን ቢሰሙ፣ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቁ፣ እነርሱ ሕዝቤ፣ እኔም አምላካቸው እንድሆን የሰጠኋቸው ቃል ነው፤
“አሁንም እንግዲህ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ጥፋትን እያዘጋጀሁላችሁ ነው፤ ክፋትንም እየጠነሰስሁላችሁ ነው። ስለዚህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ተግባራችሁን አቅኑ።” ’
“ታዲያ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስም ሆነ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ገደሉትን? ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን ፈርቶ ምሕረት አልለመነምን? እግዚአብሔርስ በእነርሱ ላይ ለማምጣት ያሰበውን ቅጣት አልተወምን? በራሳችን ላይ እኮ ታላቅ ጥፋት እያመጣን ነው።”
አገልጋዮቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ወደ እናንተ ላክሁ፤ እነርሱም፣ “እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ምግባራችሁን አስተካክሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖሩ ዘንድ ሌሎቹን አማልክት ለማገልገል አትከተሉ” አልኋችሁ። እናንተ ግን ጆሯችሁን ወደ እኔ አላዘነበላችሁም፤ አልሰማችሁኝምም።
ምናልባትም የይሁዳ ሕዝብ ላመጣባቸው ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ ሲሰሙ፣ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ክፋታቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”
ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “አሳልፈው አይሰጡህም፤ ብቻ የምነግርህን የእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፤ መልካም ይሆንልሃል፤ ሕይወትህም ትተርፋለች።
እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ! ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ! የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’
በምሕረቱ ተመልሶ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የሚሆነውን፣ የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን እንዲተርፋችሁ፣ በረከቱን ይሰጣችሁ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?
ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁትስ ይህን አልነበረምን? ፈጥኜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የተነሣሁትም ለዚሁ ነበር፤ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣ የዘገየህ አምላክ፣ ምሕረትህ የበዛ፣ ጥፋትንም ከማምጣት የምትመለስ እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ።
እግዚአብሔር መሳፍንትን ባሰነሣላቸው ቍጥር ከመስፍኑ ጋራ ስለሚሆን፣ እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው ያድናቸው ነበር፤ ከጠላቶቻቸው ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው በሚጮኹበት ጊዜ እግዚአብሔር ይራራላቸው ነበር።