ዮናስ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምዮናስ ወደ ነነዌ ሄደ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤ 2 “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።” 3 ዮናስም የእግዚአብሔርን ቃል ታዘዘ፤ ወደ ነነዌም ሄደ። በዚህ ጊዜ ነነዌ ታላቅ ከተማ ነበረች፤ እርሷንም ከዳር እስከ ዳር ለመጐብኘት ሦስት ቀን ያስፈልግ ነበር። 4 ዮናስም ወደ ከተማዪቱ ገብቶ የመጀመሪያውን ቀን ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ዐወጀ። 5 የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ። 6 ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ በደረሰ ጊዜ፣ ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሱንም አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ በዐመድ ላይ ተቀመጠ። 7 ከዚያም እንዲህ ሲል በነነዌ ዐዋጅ አስነገረ፤ “ከንጉሡና ከመሳፍንቱ የወጣ ዐዋጅ፤ “ማንም ሰው ወይም እንስሳ፣ የከብት መንጋም ሆነ የበግ መንጋ፣ ምንም ነገር አይቅመስ፤ አይብላ፤ ውሃም አይጠጣ። 8 ነገር ግን ሰውም እንስሳም ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ ሰዎችም ሁሉ ክፉ መንገዳቸውንና የግፍ ሥራቸውን ይተዉ። 9 እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ራርቶ ከጽኑ ቍጣው ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” 10 እግዚአብሔርም ምን እንዳደረጉና ከክፉ መንገዳቸውም እንዴት እንደ ተመለሱ ባየ ጊዜ ራራላቸው፤ በእነርሱም ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት አላደረገም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.