ዘሌዋውያን 13:5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው መገታቱን ቢያይ፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ፥ አሁንም ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቍስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ካህኑ በሰባተኛው ቀን እንደገና ይመርምረው፤ በሚመረምረውም ጊዜ ቊስሉ ምንም ለውጥ ሳያሳይ እንደ ነበረ ሳይስፋፋ ቢያገኘው፥ አሁንም ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያችን ደዌ ይያት፤ እነሆም፥ ያች ደዌ በፊት እንደ ነበረች ብትሆን፥ በቆዳውም ላይ ባትሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይለየዋል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል። |
ነገር ግን ቋቁቻው በሰውነቱ ቆዳ ላይ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ በእርሱም ላይ ያለው ጠጉር ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል።
በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ዳግም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል።
የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጉሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል።