Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሥጋ ደዌ ዓይነቶቹ እና ምልክቶቹ

1 ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦

2 ማናቸውም ሰው በሰውነቱ ቆዳ ላይ እባጭ ወይም ብጉር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሰውነቱ ቆዳ እንደ ለምጽ ደዌ ቢሆን፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ከልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት።

3 ካህኑም በሰውነቱ ቆዳ ላይ ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ከሰውነቱ ቆዳ በታች ዘልቆ ቢታይ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ፦ ርኩስ ነው ይበለው።

4 ነገር ግን ቋቁቻው በሰውነቱ ቆዳ ላይ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ በእርሱም ላይ ያለው ጠጉር ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል።

5 በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው መገታቱን ቢያይ፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ፥ አሁንም ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል።

6 በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ዳግም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል።

7 ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥ እንደገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል።

8 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው።

9 ማናቸውም ሰው በለምጽ ደዌ ቢጠቃ እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡታል፤

10 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቆዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢኖር፥ በእርሱም ላይ ያለውን ጠጉር ለውጦት ቢያነጣው፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥

11 እርሱ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የቈየ የለምጽ ደዌ ነው፥ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይለየውም።

12 ለምጹም በቆዳው ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ካህኑ ማየት እስከሚችልበት አካል የለምጹ ደዌ የታመመውን ሰው ቆዳ ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ ቢሸፍነው፥

13 ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ሰውነቱን ሁሉ ቢሸፍነው የታመመውን ሰው፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሰውነቱ ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው።

14 የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል።

15 ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ የለምጽ ደዌ ነውና ርኩስ ነው።

16 የሚያዠው ሥጋ ግን ተለውጦ ቢነጣ እንደገና ወደ ካህኑ ይመጣል።

17 ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው።

18 በሰውነቱም ቆዳ ላይ የዳነ የብጉንጅ ቁስል ቢኖር፥

19 በብጉንጁም የቁስል ስፍራ ላይ ነጭ እባጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል።

20 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከብጉንጁ ቁስል ውስጥ ወጥቶአል።

21 ካህኑም ቢያየው፥ እነሆም፥ በእርሱ ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖርበት፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል።

22 በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው።

23 ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የብጉንጅ ቁስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።

24 “በሰውነቱም ቆዳ ላይ የእሳት ቃጠሎ ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣበት፥

25 ካህኑ ያየዋል፥ እነሆም፥ በቋቁቻው ላይ ያለው ጠጉር ተለውጦ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው።

26 ነገር ግን ካህኑ ቢያየው፥ በቋቁቻውም ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖር፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል።

27 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው።

28 ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የቃጠሎው እባጭ ነው፤ የቃጠሎውም ጠባሳ ነውና ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።

29 “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራስ ወይም በአገጭ ላይ ደዌ ቢኖርባቸው፥

30 ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳው በታች ዘልቆ ቢታይ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጉር ቢኖርበት፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ የለምጽ ደዌ ነው።

31 ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ጥቁርም ጠጉር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል።

32 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጉር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ከቆዳው በታች ባይዘልቅ፥

33 ይላጫል፥ ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ አሁንም ካህኑ ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል።

34 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል።

35 ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥

36 ካህኑ ያየዋል፤እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጉር አይፈልግም፤ እርሱ ርኩስ ነው።

37 ቈረቈሩ ግን መገታቱን ቢያይ፥ ጥቁርም ጠጉር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ድኖአል፤ እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።”

38 “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርባቸው፥

39 ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ያለው ቋቁቻ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቢሆን በቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ነው፤ ከቆዳው ውስጥ ወጥቶአል፤ እርሱ ንጹሕ ነው።

40 “የሰውም ጠጉር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው።

41 ጠጉሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው።

42 ዳሩ ግን በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ የለምጽ ደዌ ነው።

43 ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የሆነ የለምጽ ደዌ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ላይ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቢሆን፥

44 በለምጽ ደዌ የተያዘ ሰው ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ካህኑ፦ በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ላይ የሚገኝ ነው።

45 “የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው የሚለብሳቸው ልብሶች የተቀደዱ ይሁኑ፥ የራሱም ጠጉር የተጐሳቈለ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ እያለ ይጩኽ።

46 በእርሱ ደዌው እስካለበት ጊዜያት ድረስ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር ውጪ ይሆናል።

47 “የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢወጣ፥ ልብሱም የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ቢሆን፥

48 በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጉር ቢሆን፥ በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ቢሆን፥

49 ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢይታ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ እዲያየው ይደረጋል።

50 ካህኑም ደዌውን ያያል፤ ደዌውም ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል።

51 በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ለማናቸውም አገልግሎት በሚውል የተለፋ ቆዳ ላይ ቢሰፋ፥ ደዌው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱም ርኩስ ነው።

52 ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ወይም ከተለፋው ቆዳ የሆነ ማናቸውም ደዌው ያለበት ነገር ላይ ቢሆን፥ እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነውና በእሳት ይቃጠል።

53 “ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ባይሰፋ፥

54 ካህኑ ደዌ ያለበን ነገር እንዲያጥቡ ያዝዛል፤ ሌላም ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል።

55 ደዌው ያለበት ነገር ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ባይሰፋ ነገር ግን መልኩን ባይለውጥ፥ እርሱ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ የለምጽ ደዌው ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው።

56 “ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ከታጠበ በኋላ ደዌው ቢከስም፥ ምልክቱ የነበረበትን ቦታ ከልብሱ ወይም ከተለፋው ቆዳ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው።

57 በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ዳግም ቢታይ፥ እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር በእሳት ታቃጥለዋለህ።

58 ነገር ግን አንተ ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ ከተሠራ ከማናቸውም ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል።

59 “ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለመወሰን እንዲቻል፥ በበግ ጠጉር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ የሚወጣ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos