ዕዝራ 3:11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ደግሞም ጌታን እያከበሩና እያመሰገኑ “ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” እያሉ ዘመሩ። ሕዝቡ ሁሉ ጌታን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ፥ ይህም የጌታ ቤት ስለ ተመሠረተ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በውዳሴና በምስጋናም ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲሉ ዘመሩ፤ “ቸር ነውና፤ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።” የእግዚአብሔር ቤት መሠረት ስለ ተጣለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በታላቅ ድምፅ እልል እያሉ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ለእስራኤል ያለውም ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” የሚለውን መዝሙር በመቀባበል ለእግዚአብሔር ክብር ዘመሩት፤ የቤተ መቅደሱ መሠረት የማኖር ተግባር ስለ ተጀመረም እያንዳንዱ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እልል በማለት እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ደግሞ፥ “ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” እያሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት በተመሠረተ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩ በታላቅ ድምፅ ዘመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ደግሞም “ቸር ነውና፤ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና” እያሉ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በእርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት ስለ ተመሠረተ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ “እልል” አሉ። |
ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን እንዲያመሰግኑ ኤማንንና ኤዶታምን፥ በስማቸውም የተጻፉትን ተመርጠው የቀሩትን ከእነርሱ ጋር በዚያ ተዋቸው።
መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው በአንድ ድምፅ ጌታን እያመሰገኑና እያከበሩ፦ “ጌታ መልካም ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና” ጌታን አመስግኑ እያሉ ድምጻቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ ጌታን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው ቤቱን፥ የጌታን ቤት ሞላው።
የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የጌታም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር፤ በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ እንዲህም ብለው ጌታን አመሰገኑ፦ “እርሱ መልካም ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና።”
የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሻብያ፥ ሼሬብያ፥ የቃድሚኤል ልጅ ኢያሱና ወንድሞቻቸው ደግሞ ከፊት ለፊታቸው ሆነው የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ክፍል በክፍል ትይዩ ሆነው ያወድሱና ያመሰግኑ ነበር።
ሰማያት ሆይ፥ ጌታ አድርጎታልና ዘምሩ፤ ጌታ ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ።
እርሱም፦ የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የሙሽራው ድምፅና የሙሽራይቱ ድምፅ፥ ወደ ጌታም ቤት፦ ‘ጌታ ቸር ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታን አመስግኑ!’ እያሉ የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ ነው። የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥ ይላል ጌታ።
ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም፦ ‘ሞገስ ይሁንለት! ሞገስ ይሁንለት!’ ብለው እየጮኹ እርሱ የመደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል” ብሎ ነገረኝ።
አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ! አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ! እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታሰሙ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ ከዚያን በኋላ ግን ትጮኻላችሁ።”
ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ እርሷ አቅንቶ በቀጥታ ይገባል።”