መዝሙር 47 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ለመዘምራን አለቃ፥ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 2 አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ። 3 ጌታ ልዑል ግሩምም ነውና፥ በምድር ሁሉ ላይም ታላቅ ንጉሥ ነውና። 4 አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን። 5 ለሚወደው ለያዕቆብ ኩራት የሆነችውን ርስታችንን እርሱ ይመርጥልናል። 6 አምላክ በእልልታ፥ ጌታ በመለከት ድምፅ ዐረገ። 7 ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፥ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። 8 እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፥ በጥበብ ዘምሩ። 9 እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ፥ እግዚአብሔር በተቀደሰው ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። 10 የአሕዛብ አለቆች፥ እንደ አብርሃም አምላክ ሕዝብ ተሰበሰቡ፥ የምድር ጋሻዎች የእግዚአብሔር ናቸውና፤ እርሱም እጅጉን ከፍ ብሏል። |