ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ቅዱሳን በእግዚአብሔር ረድኤት እንደሚጠበቁ 1 የጻድቃን ነፍስ ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት፤ መከራም አያገኛቸውም። 2 በሰነፎች ዓይኖች ግን የሞቱ መሰሉ፤ በሞትም ከዚህ ዓለም መውጣታቸው ክፋት እንዳለባቸው ተቈጠረ። 3 ሞታቸውም ጥፋት መሰለ፤ እነርሱ ግን በሰላም አሉ። 4 በሰው ፊትም ቢፈረድባቸው ተስፋቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞት የሌለባት ፍጽምት ሕይወት ናት። 5 ጥቂት መከራ ተቀብለው ብዙ ክብር ያገኛሉ። እግዚአብሔር ፈትኗቸው ለእርሱ የተገቡ ሆነው አግኝትዋቸዋልና። 6 ወርቅ በከውር እንዲፈተን ፈተናቸው፤ እንደሚቃጠል መሥዋዕትም ተቀበላቸው። 7 በሚጐበኙበትም ወራት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ በብርዕ ላይ የወደቀ የእሳት ፍንጣሪ እንዲሰፋ በክብር እየሰፉ ይሄዳሉ። 8 አሕዛብን ይገዛሉ፤ በሕዝብም ላይ ይሠለጥናሉ፤ እግዚአብሔርም ለዘለዓለም ይነግሥላቸዋል። 9 በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች እውነትን ያውቃሉ፤ ጸጋና ምሕረት ለመረጣቸው ነውና፥ የተገለጠ ጕብኝቱም ለጻድቃኑ ነውና ምእመናን በእርሱ ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች በክፋታቸው እንደሚጐዱ 10 ክፉዎች ሰዎች ግን እንዳሰቡ ክፉ ፍርድን ያገኛሉ፥ እውነትንም ያቀለሉ ሰዎች ከእግዚአብሔር ራቁ። 11 ጥበብንና ተግሣጽን የሚንቁ ሰዎች ጐስቋሎች ናቸው፤ አለኝታቸው ከንቱ ነው፤ ድካማቸውም፥ መከራቸውም ጥቅም የሌለው ነው፤ ሥራቸውም ከንቱ ነው፤ 12 ሚስቶቻቸውም ሰነፎች ናቸው፤ ልጆቻቸውም ጠማሞች ናቸው፤ ትውልዳቸውም የተረገመ ነው። በንጽሕና ስለመኖር 13 ነውር የሌለባት፥ የኀጢአት ምንጣፍ የማታውቅ መካን ሴት ብፅዕት ናት፥ ከኀጢአትም የነጻች ናት፥ ይህች እንዲህ ያለችው ሴት ነፍሳት በሚጐበኙበት ጊዜ ፍሬ ታገኛለች። 14 የተመረጠች የሃይማኖት ዋጋ ትሰጠዋለችና፥ በሚወደድ በእግዚአብሔርም ቤት ዕድሉ ይሰጠዋልና በእጁ በደልን ያልሠራ፥ በእግአብሔርም ላይ ክፉ ነገርን ያላሰበ ጃንደረባም ብፁዕ ነው። 15 የደግ ሰው የድካሙ ፍሬ ክብርና ጌጥ ነው፤ ለዕውቀቱም ሥር ውድቀት የለበትም። 16 ያመንዝራዎች ልጆች ግን ከቍጥር የጐደሉ ይሆናሉ። ከሕግ ተላላፊ መኝታ የተወለደ ልጅም ይጠፋል። 17 ኑሮአቸውም በምድር ላይ ቢበዛ ምንም አይቈጠርም፤ ሽምግልናቸውም በፍጻሜያቸው የጐሰቈለ ይሆናል። 18 ፈጥነውም ቢሞቱ በፍርድ ቀን ተስፋና መጽናናት አይኖራቸውም። 19 ለዐመፀኛ ትውልድ ፍጻሜዋ ክፉ ነውና። |