Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)

1 ለተሳዳቢና ለሰካራም ወይን ክፉ ነው፥ ጽዋውንም መላልሶ የሚጨልጥ ጠቢብ አይደለም፥ እንደዚህ ያለ አላዋቂም ሁሉ አንድ ይሆናል።

2 የንጉሥ ቍጣ ከአንበሳ ቍጣ አያንስም፤ የሚያስቈጣውም ሰው የራሱን ነፍስ ይበድላል።

3 የሰው ክብሩ ከስድብ መከልከል ነው፤ ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል።

4 ታካች ሰው ሲያሽሟጥጡት አያፍርም፤ ስለዚህ በመከር ጊዜ ይለምናል፥ የሚሰጠውም የለም። በክምሩ እያለ ስንዴ የሚበደር እንደዚሁ ነው።

5 ምክር በሰው ልብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።

6 ይቅር ባይ ሰው ታላቅና ክቡር ነው፤ ነገር ግን የታመነ ሰው የሚገኘው በድካም ነው።

7 ያለ ነውር ወደ እውነት በንጹሕ የሚሄድ፥ ልጆቹን ብፁዓን ያደርጋቸዋል።

8 እውነተኛ ንጉሥ በዙፋኑ በተቀመጠ ጊዜ በዐይኖቹ ፊት ምንም ክፉ አይቃወመውም።

9 ንጹሕ ልብ አለኝ ብሎ የሚመካ ማን ነው? ከኀጢአትስ ንጹሕ ሆኖ የሚታይ ማን ነው?

10 ሁለት ዐይነት ሚዛንና ሁለት ዐይነት መስፈሪያ፥ ሁለቱ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሳን ናቸው። የሚሠራቸውም በሥራው ይሰነካከላል።

11 የእውነተኛ ጐልማሳ መንገዱ የቀና ነው።

12 የሚሰማ ጆሮና የሚያይ ዓይን፥ ሁለቱ የእግዚአብሔር ሥራ ናቸው።

13 እንዳትወገድ ማማትን አትውደድ። ድሃም እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ ዐይንህን ክፈት፥ እንጀራም ትጠግባለህ።

14 የሚገዛ ሰው፦ “ክፉ ነው፥ ክፉ ነው” ይላል፤ በሄደ ጊዜ ግን ይመካል።

15 ወርቅና ብዙ ቀይ ዕንቍ ይገኛል፤ የዕውቀት ከንፈር ግን የከበረች ጌጥ ናት።

16 ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው።

17 የሐሰት እንጀራ ለሰው የጣፈጠ ነው፤ ከዚህ በኋላ ግን አፉ ጭንጫ ይሞላል።

18 ዐሳብ በምክር ትጸናለች፥ በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ።

19 ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል፤ በከንፈሩ የሚያባብል ሰውን አትገናኘው።

20 አባቱንና እናቱን የሚያማ ብርሃኑ ይጠፋል፥ የዐይኖቹ ብሌንም ጨለማን ያያል።

21 አስቀድሞ ለርስት የሚቸኩል፥ በፍጻሜው አይባረክም።

22 ጠላቴን እበቀለዋለሁ አትበል፤ ነገር ግን እንዲረዳህ እግዚአብሔርን ተማመን።

23 ሁለት ዓይነት ሚዛን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ ሐሰተኛ ሚዛንም መልካም አይደለም።

24 የሰው አካሄዱ በእግዚአብሔር ዘንድ ይቃናል፤ ሟች ግን መንገዱን እንዴት ያውቃል?

25 ሰው ከገንዘቡ በችኮላ የተቀደሰ ነው ብሎ ቢሳል፥ ከተሳለም በኋላ ቢፀፀት ወጥመድ ይሆንበታል።

26 ብልህ ንጉሥ የኃጥኣን መንሽ ነው፥ በእነርሱ ላይም መንኰራኵርን ይነዳባቸዋል።

27 የሰው መንፈስ የሆድን መዛግብት የሚመረምር፥ የእግዚአብሔር መብራት ነው።

28 ቸርነትና እውነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤ ዙፋኑንም በእውነት ይከቡታል።

29 ለጐልማሶች ጌጣቸው ጥበብ ነው። ለሽማግሌዎችም ክብራቸው ሽበት ነው።

30 ሽብርና ስደት ክፉዎችን ድንገት ይገናኛቸዋል፥ ግርፋትም ወደ ሆድ ዕቃ ይገባል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች