ቈላስይስ 2:15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ በመስቀሉ ድል በመንሣት እነርሱን በይፋ አጋለጣቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የገዦችና የባለሥልጣናትንም ማዕርግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኀይሎችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነሥቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አለቆችንና ገዢዎችን በመግፈፉ በግልጥ አሳያቸው፤ ራቁቱን በመሆኑም አሳፈራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። |
ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአል፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።
ወይስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን እንዴት መዝረፍ ይችላል? ካሰረው በኋላ ግን ቤቱን ይዘርፋል።
እንደ እነርሱ ከሆነ የማያምኑ ሰዎችን ልቦና፥ የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ አሳውሯል።
ተጋድሏችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ነገር ግን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፥ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው።
የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤
እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፥ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ እርሱም ዲያብሎስ ነው።
ታላቁም ዘንዶ ወደ ታች ተጣለ፤ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።
ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያሉ።