ሉቃስ 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ኢየሱስ ስለ ጸሎት ማስተማሩ ( ማቴ. 6፥9-13 ፤ 7፥7-11 ) 1 እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንዲሁ መጸለይን አስተምረን፤” አለው። 2 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በማናቸውም ጊዜ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባት ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ 3 የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ 4 ኀጢአታችንንም ይቅር በለን፤ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር እንላለንና፤ ወደ ፈተናም አታግባን።’ ” 5 እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ ማን ይሆን ወዳጅ ኖሮት፥ በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ እንዲህ የሚለው፦ ‘ወዳጄ ሆይ! ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ 6 አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት ምንም የለኝምና’፤ 7 ያም ከውስጥ መልሶ፦ ‘አታስቸግረኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ናቸው፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም፤’? 8 እላችኋለሁ፤ ወዳጁ ስለ ሆነ እንኳ ተነሥቶ ባይሰጠው፥ ስለ ንዝነዛው ግን ተነሥቶ የሚፈልገውን ያህል ይሰጠዋል። 9 እኔም እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ 10 የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። 11 አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ ዓሣ ቢለምነው፥ በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? 12 ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? 13 እንግዲያውስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው!” ዓይነ ስውርና መናገር የተሳነው ጋኔን ስለያዘው ሰው ( ማቴ. 12፥22-30 ፤ ማር. 3፥20-27 ) 14 መናገርም የተሳነውን ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣ በኋላ መናገር የተሳነው ሰው ተናገረ፥ ሕዝቡም ተደነቁ፤ 15 ከእነርሱ ዘንድ አንዳንዶች ግን፦ “በብዔልዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል፤” አሉ። 16 ሌሎችም ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። 17 ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የተለያየ መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል። 18 ሰይጣንም ደግሞ እርስ በርሱ ቢለያይ መንግሥቱ እንዴት ይቆማል? እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ እናንተ ብላችኋልና፤ 19 እኔስ በብዔልዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ፥ ልጆቻችሁ በማን ያስወጣሉ? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። 20 እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥቷል። 21 በማናቸውም ጊዜ ኀይለኛ ሰው በሚገባ የጦር ዕቃውን ታጥቆ የራሱን ግቢ ቢጠብቅ፥ ያለው ንብረቱ በሰላም የተጠበቀ ይሆናል፤ 22 ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ አደጋ ጥሎበት ካሸነፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን የጦር ዕውቃን ይወስድበታል፤ ምርኮውንም ያካፍላል። 23 ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋርም የማይሰበስብ ይበትናል። ስለ ርኩሳን መናፍስት 24 “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን ፈልጎ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባለማግኘቱ ግን፦ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤ 25 ሲመጣም ተጠርጎና ተስተካክሎ ያገኘዋል። 26 በዚያም ጊዜ ሄዶ ከእርሱ የባሱ ክፉ ሌሎች ሰባት መናፍስትን ከእርሱ ጋር ያመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ የዚያም ሰው ሁኔታ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆናል።” እውነተኛ ደስታ 27 ኢየሱስም ይህንን በመናገር ላይ ሳለ፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፦ “የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው፤” አለችው። 28 እርሱ ግን፦ “በእርግጥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው፤” አለ። ምልክትን ስለ ጠየቁ ሰዎች ( ማቴ. 12፥38-42 ) 29 ሕዝብም በብዛት እየተሰበሰቡ በነበሩ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር፦ “ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው፤ ምልክትን ይፈልጋል፤ ከዮናስም ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። 30 ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። 31 ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ትነሳለች፥ በእነርሱም ላይ ትፈርዳለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ በዚህ አለ። 32 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ይነሳሉ፥ በእርሱም ላይ ይፈርዳሉ፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ በዚህ አለ። የሰውነት መብራት ( ማቴ. 5፥15 ፤ 6፥22-23 ) 33 “መብራትንም አብርቶ በስውር ቦታ ወይም ከእንቅብ በታች የሚያኖረው ማንም የለም፤ የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። 34 የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው። ዐይንህ ጤናማ በሆነ ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ በብርሃን የተመላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ በሆነ ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ በጨለማ የተመላ ይሆናል። 35 ስለዚህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳልሆነ በልብህ አስተውል። 36 እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ በብርሃን የተመላ፥ ጨለማም የሆነ የአካል ክፍል የሌለው ከሆነ፥ መብራት በፀዳሉ ብርሃን እንደሚሰጥህ እንዲሁ ሰውነትህ ሁሉ በብርሃን የተመላ ይሆናል።” ፈሪሳውያንና የሙሴ ሕግ መምህራን መወቀሳቸው ( ማቴ. 23፥1-36 ፤ ማር. 12፥38-40 ) 37 ይህንንም በመናገር ላይ በነበረ ጊዜ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ኢየሱስም ወደ እርሱ ገብቶ ተቀመጠ። 38 ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ በማየቱ ፈሪሳዊው ተደነቀ። 39 ጌታም እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል። 40 እናንተ ሞኞች! የውጭውን የፈጠረ እርሱ የውስጡንስ ደግሞ አለፈጠረምን? 41 ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። 42 “ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ታወጣላችሁ፤ ፍርድንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ግን ቸል ትላላችሁ፤ ይልቁንስ እነዚያን ደግሞ ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ ይገባችሁ ነበር። 43 እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! በምኵራቦች የከበሬታን ወንበርንና በገበያ ቦታዎች ሰላምታን ትወዳላችሁና። 44 እናንተ ወዮላችሁ! ሰዎች ሳያውቋቸው በላያቸው የሚሄዱባቸው የተሰወሩ መቃብሮች ትመስላላችሁና።” 45 ከሕግ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ፦ “መምህር ሆይ! ይህን ስትል እኮ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው፤” አለው። 46 እርሱም እንዲህ አለ፦ እናንተ ሕግ አዋቂዎች ደግሞ ወዮላችሁ! ለመሸከም ከባድ የሆነውን ሸክም ሰዎችን ታሸክማላችሁ፥ ራሳችሁ ግን በአንዲት ጣታችሁ እንኳ ሸክሙን አትነኩትምና። 47 እናንተ ወዮላችሁ!አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብሮች ትሠራላችሁና። 48 እንግዲህ በአባቶቻችሁ ሥራ ትስማማላችሁ፤ ስለ እርሱም ትመሰክራላችሁ፤ እነርሱ ገደሉአቸው እናንተ ደግሞ መቃብሮቻቸውን ትሠራላችሁና። 49 ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፦ “ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፤ ከእነርሱም ይገድላሉ፤ ያሳድዳሉም፤ 50 ስለዚህም ይህ ትውልድ ተጠያቂ የሚሆነው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በፈሰሰው በነቢያት ሁሉ ደም፥ 51 ይህም ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ነው። አዎን እላችኋለሁ፤ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል። 52 እናንተ ሕግ አዋቂዎች ወዮላችሁ! የዕውቀትን መክፈቻ ወስዳችኋልና፤ ነገር ግን እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ የሚገቡትንም ከለከላችሁ።” 53 እርሱም ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ ጻፎችና ፈሪሳውያን እርሱን እጅግ በመቃወም ስለ ብዙ ነገሮች የትንኮሳን ጥያቄ ይጠይቁት ጀመር፤ 54 በዚህም እርሱ ከሚናገረው አንድ ነገርን ለማጥመድ አደቡበት። |