Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኤፌሶን 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ስለ ልጆችና ስለ ወላጆች

1 ልጆች ሆይ! ተገቢ ነውና ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ።

2 “አባትህንና እናትህን አክብር፤” ከተስፋ ቃል ጋር የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፤

3 “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም”

4 እናንተም አባቶች ሆይ! ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው።


ስለ አገልጋዮችና ስለ ጌቶች

5 አገልጋዮች ሆይ! ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ፥ በልባችሁ ቅንነት በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤

6 የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባርያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ።

7 ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታገለግሉ በጽኑ ፍላጎት ተገዙ፤

8 ባርያም ሆነ ነጻ ሰው፥ እያንዳንዱ ለሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ ብድራቱን እንደሚቀበል ታውቃላችሁ።

9 እናንተም ጌቶች ሆይ! ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንደማያዳላ ታውቃላችሁ።


የእግዚአብሔር የጦር መሣሪያ

10 በተረፈ በጌታ በኃይሉ ብርታትም ጠንክሩ።

11 የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም እንድትችሉ፥ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ።

12 ተጋድሏችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ነገር ግን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፥ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው።

13 ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር ትጥቅ አንሡ።

14 እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥

15 የሰላም ወንጌል ለማወጅ በዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤

16 በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤

17 የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የመዳንንም ራስ ቁር፥ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ።

18 በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ እስከ መጨረሻው በጽናት ትጉ።

19 ቃል እንዲሰጠኝና አፌን በመክፈት የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ፥ ስለ እኔም ለምኑ።

20 ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንኩ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጽ እድናገር ለምኑ።


የመጨረሻ ሰላምታ

21 እናንተ ደግሞ በምን ሁኔታ እንዳለሁና እንዴት እንደምኖር እንድታውቁት የተወደደ ወንድምና በጌታ የታመነ አገልጋይ ቲኪቆስ ሁሉን ይነግራችኋል፤

22 ስለ እኛ ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ወደ እናንተ የምልከው በዚህ ምክንያት ነው።

23 ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን።

24 ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች