Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ማቴዎስ 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ስለ ሰንበት የቀረበ ጥያቄ
( ማር. 2፥23-28 ፤ ሉቃ. 6፥1-5 )

1 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀመዛሙርቱ ተራቡና እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር።

2 ፈሪሳውያን ይህንን አይተው “እይ! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ያደርጋሉ፤” አሉት።

3 እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን?

4 ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ካህናት ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት በላ።

5 በሰንበታት በቤተ መቅደስ ያሉ ካህናት ሰንበትን እንደሚያረክሱ ንጹሐንም እንደ ሆኑ በሕጉ አላነበባችሁምን?

6 እላችኋለሁ፥ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

7 ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ ንጹሐኑን ባልኮነናችሁ ነበር።

8 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”


ኢየሱስ እጀ ሽባውን እንደ አዳነ
( ማር. 3፥1-6 ፤ ሉቃ. 6፥6-11 )

9 ከዚያ አልፎ ወደ ምኵራባቸው ገባ።

10 እነሆ አንድ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ሊከሱትም ፈልገው “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት።

11 እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው በሰንበት ወደ ጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ማነው?

12 ታዲያ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል።”

13 ከዚያ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም ዘረጋት፤ ያንጊዜ እንደ ሁለተኛዋ ደህና ሆነች።

14 ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ተማከሩ።

15 ኢየሱስ ይህንን አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው።

16 እንዳያጋልጡትም አዘዛቸው፤

17 ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤

18 “እነሆ የመረጥሁት አገልጋዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያውጃል።

19 አይከራከርም አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም።

20 ፍርድን ወደ ድል እስኪያመጣ ድረስ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስን የጧፍ ክር አያጠፋም።

21 አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”


ኢየሱስና ብዔልዜቡል
( ማር. 3፥20-30 ፤ ሉቃ. 11፥14-23 )

22 ከዚህ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ዲዳ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ዲዳውም ተናገረ አየም።

23 ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።

24 ፈሪሳውያን ግን ይህን ሰምተው “ይህ በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ።

25 እርሱ ግን ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እርስ በርስዋ የምትከፋፈል መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤ እርስ በርስዋ የምትከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁላ አትቆምም።

26 ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት መቆም ይችላል?

27 እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል የማስወጣ ከሆነ፥ ልጆቻችሁ በማን ያስወጡአቸዋል? በዚህም ምክንያት እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።

28 እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማስወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች።

29 ወይስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን እንዴት መዝረፍ ይችላል? ካሰረው በኋላ ግን ቤቱን ይዘርፋል።

30 ከእኔ ጋር ያልሆነ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብ ደግሞ ይበትናል።

31 በዚህም ምክንያት እላችኋለሁ፤ ሰው ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስን የሰደበ ግን አይሰረይለትም።

32 በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።

33 “ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፤ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ፤ ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና።

34 እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ የሞላውን አፍ ይናገራልና።

35 መልካም ሰው ከመልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።

36 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤

37 ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፥ ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህና።”


ተአምራት ለማየት የቀረበ ጥያቄ
( ማር. 8፥11-12 ፤ ሉቃ. 11፥29-32 )

38 በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና “መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት።

39 እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።

40 ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁም የሰው ልጅ በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል።

41 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤ እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

42 የደቡብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።


የርኩስ መንፈስ በሰው ውስጥ ተመልሶ መግባት
( ሉቃ. 11፥24-26 )

43 “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ አያገኝምም።

44 በዚያን ጊዜ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ ሲመጣም ባዶ ሆኖ፥ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል።

45 ከዚያ ይሄድና ከእርሱ የከፉ ሰባት ሌሎች አጋንንትን ከእርሱ ጋር ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ የሰውየው መጨረሻ ከፊተኛው ይልቅ የከፋ ይሆናል። ለዚህም ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።”

46 ለሕዝቡ ይህን እየተናገረ ሳለ፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።

47 አንድ ሰውም “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።

48 እርሱ ግን ለነገረው መልሶ እንዲህ አለው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው።

49 እጁንም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤

50 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴም እናቴም ነውና።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች