Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ቆሮንቶስ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ስለዚህ ዳግመኛ በጉብኝቴ እንዳላስቸግራችሁ ወደ እናንተ ላለመምጣት ቆረጥሁ።

2 እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው?

3 ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ስለምተማመን፥ ደስ ሊያሰኙኝ ወደሚገባቸው በመምጣቴ ማስቸገር እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍኩላችሁ።

4 በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት፥ በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበር፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም።


ለበደለኛ ይቅርታ ስለ ማድረግ

5 ነገር ግን ማንም ያሳዘነ ቢኖር፥ እኔን ብቻ ሳይሆን ያሳዘነው፥ ባላጋንነው በተወሰነ መልኩ፥ ሁላችሁንም ነው።

6 እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ በብዙሃኑ ስለተቀጣ በቂው ነው።

7 ከልክ በላይ አዝኖ ተስፋ እንዳይቆርጥ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል።

8 ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅራችሁን መልሳችሁ እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ።

9 በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን ለማወቅ በማሰብ፥ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበር።

10 እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፤

11 ይህን የምናደርገው በሰይጣን መበለጥ እንዳንችል ነው፤ ማናችንም የእርሱን አሳብ አንስተውም።


ስለ አዲስ ኪዳን አገልጋዮች

12 የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ በጌታ በሩ ተከፍቶልኝ ነበር፤

13 ነገር ግን መንፈሴ ማረፍ አልቻለም፤ ምክንያቱም እዚያ ወንድሜን ቲቶን አላገኘሁትም። ስለዚህ ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ።

14 ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን፥ በእኛም በሁሉም ስፍራ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ፥ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።

15 በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነን፤

16 ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፥ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?

17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚነግዱ እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች