Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ያንጊዜ ጻድቁ፦ መከራ ባጸኑበትና ድካሙን በካዱ፥ ነገሩንም በናቁ ሰዎች ፊት በብዙ መገለጥ ይቆማል። 2 በግርማና በክፉ ማስፈራራት ሆኖ ባዩት ጊዜ ይታወካሉ፤ ድንቅ ስለሚሆን ደኅንነቱም ይደነቃሉ። 3 እየተጸጸቱና በተጨነቀ መንፈስ እየጮኹ እርስ በርሳቸው ይናገራሉ፦ እንዲህም ይላሉ፥ “ቀድሞ በኛ በሰነፎች ዘንድ መሣቂያና ማሽሟጠጫ የሆነው፥ 4 ሥራውን ስንፍና፥ ሞቱንም የተናቀ ያደረግንበት ይህ ነውን? 5 እንዴት የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ? ርስቱስ እንዴት ለቅዱሳን ሆነች? 6 ስለዚህ ከቀና መንገድ ወጥተን ስተናል፥ የጽድቅ ብርሃንም አልተገለጠልንም፥ ፀሐይም አልወጣልንም። 7 በደልንና ጥፋትን በመንገዳችን ሞላን፤ በምድረ በዳም ሄድን፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ አላወቅንም። 8 “ትዕቢት ምን ጠቀመን? ከትዕቢት ጋር ያለ ባለጠግነትስ ምን አመጣልን? 9 ይህ ሁሉ እንደ ጥላ ኀላፊ ነው፤ ፈጥኖም እንደሚሄድ ወሬ ነው። 10 በባሕር ላይ እንደሚሄድ፥ ውኃም በማዕበሉ እንደሚነጥቀው፥ ያለፈበት ፍለጋው እንደማይገኝ፥ በማዕበሉም መካከል አካሉ የሄደበት መንገድ እንደማይታወቅ መርከብ፥ 11 በአየር ላይ የሚበርር ዎፍ የሄደበት ፍለጋው እንደማይገኝ፥ በበረረ ጊዜ ቀላሉን አየር እየከፈለ ፈጥኖ ይሄዳልና፥ ክንፉንም እያርገበገበ፥ ፈጥኖ ይበርራልና ከሄደም በኋላ በነፋሱ ውስጥ ያለፈበት ምልክቱ እንደማይገኝ፥ 12 ይህም ባይሆን የተወረወረ ፍላፃ ሰንጥቆት ያለፈው አየር ተመልሶ እንደሚገጥም፥ በአየር ውስጥ የሄደበትም እንደማይታወቅ፥ 13 እኛም እንዲሁ ነን፤ በተወለድን ጊዜ ጠፋን። በክፋታችን ጠፋን እንጂ በጎ ምልክትን እናሳይ ዘንድ አልተገባንም።” 14 የክፉዎች ሰዎች ተስፋቸው ነፋስ እንደሚበትነው ትቢያ፥ በነፋስ ቀልጦ እንደሚጠፋ ረቂቅ ውርጭ፥ በነፋስም ተበትኖ እንደሚጠፋ ጢስ፥ አንድ ቀንም አድሮ እንደሚሄድ መጻተኛ ስም አጠራር ነው። ጻድቃን የሚያገኙትዋጋ 15 ጻድቃን ግን ለዘለዓለም ይኖራሉ፤ ዋጋቸውም በእግዚአብሔር ዘንድ የጸና ነው፤ ጥበቃቸውም በልዑል ዘንድ ነው። 16 ስለዚህም የክብር መንግሥትንና ጌጥ ያለው አክሊልን ከእግዚአብሔር እጅ ይቀበላሉ፤ በቀኙ ይሰውራቸዋልና፥ በክንዱም ይረዳቸዋልና። 17 ፍጹም የሆነ የቅንዐቱን ጦር መሣሪያ ይይዛል፤ ጠላቶቹንም ለመበቀል ፍጥረቱን የጦር መሣሪያ ያደርጋታል። 18 የጽድቅ ጥሩርንም ይለብሳል፥ ማድላት የሌለበት የፍርድ ራስ ቍርንም ይቀዳጃል። 19 የማይሸነፍ የእውነት ጋሻንም ይይዛል። 20 መዓቱንም እንደሚቈርጥ ሰይፍ ይስላል፤ ዓለምም ከእርሱ ጋር ሆኖ አላዋቂዎችን ይዋጋል። 21 ፈጥኖ ያገኛቸው ዘንድ በአሳቾች ሰዎች ላይ የመብረቆቹ ድል ነጎድ በቀጥታ ይሄድባቸዋል። መልካም ሆኖ ከተገተረ ቀስት እንደሚወረወር ፍላጻ ከደመናዎች ውስጥ ወደ ዓላማቸው ይወረወራሉ ። 22 ከመዓቱ ድል ነጎድ ደንጊያም ፈጥኖ በረዶን ያወርዳል፤ የባሕሩም ውኃ በእነርሱ ላይ ይበሳጭባቸዋል፤ ፈሳሾችም ይነዋወጣሉ፤ ፈጥነውም ይከቧቸዋል። 23 ኀይል ያለው ነፋስም ይቃወማቸዋል፤ እንደ ነፋስም ያደርቃቸዋል፤ ኀጢአት ምድሩን ሁሉ ታጠፋለችና፥ ክፉም መሥራት የኀያላኑን ዙፋን ይገለብጣልና ይበትናቸዋል። |