ነህምያ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤላውያን ከአሕዛብ መለየታቸው 1 በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ፤ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘለዓለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ አገኙ። 2 የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ አልተቀበሉአቸውምና፥ ይረግማቸውም ዘንድ በለዓምን ገዝተውባቸዋልና፤ ነገር ግን አምላካችን ርግማኑን ወደ በረከት መለሰው። 3 ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ከእስራኤል ጋር የተደባለቀውን ሕዝብ ሁሉ ለዩ። 4 ከዚህም አስቀድሞ በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሾሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሴብ ከጦብያ ጋር ተወዳጅቶ፥ 5 ለሌዋውያን፥ ለመዘምራንና ለበረኞቹ እንደ ሕጉ የተሰጣቸውን የእህሉን ቍርባንና ዕጣኑን፥ ዕቃዎቹንም፥ የእህሉንና የወይኑን፥ የዘይቱንም ዐሥራት፥ ለካህናቱም የሆነውን ቀዳምያቱን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን ታላቅ ዕቃ ቤት አዘጋጅቶለት ነበር። 6 እኔ ግን በባቢሎን ንጉሥ በአርተሰስታ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበርና በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም። ከጥቂት ዘመንም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ለመንሁ፤ 7 ወደ ኢየሩሳሌምም መጣሁ፤ ኤልያሴብም በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦቢያ ዕቃ ቤቱን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ። 8 እጅግም አስከፋኝ፤ የጦብያንም የቤቱን ዕቃ ሁሉ ከዕቃ ቤት ወደ ውጭ ጣልሁ። 9 ዕቃ ቤቶቹንም እንዲያነጹ አዘዝሁ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃዎች፥ የእህሉንም ቍርባን፥ ዕጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ። 10 ለሌዋውያንም ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፥ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደ ሄደ ተመለከትሁ። 11 እኔም፥ “የእግዚአብሔር ቤት ስለ ምን ተተወ?” ብዬ ከአለቆቹ ጋር ተከራከርሁ። ሰበሰብኋቸውም፤ በየስፍራቸውም አቆምኋቸው። 12 ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም ዐሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ። 13 በዕቃ ቤቶችም ላይ ካህኑን ሰሌምያን፥ ጸሓፊውንም ሳዶቅን፥ ከሌዋውያኑም ፈዳያን ሾምሁ፤ ከእነርሱም ጋር የመታንያ ልጅ የዘኩር ልጅ ሐናን ነበረ፤ እነርሱም የታመኑ ሆነው ተገኙ፤ ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው ማከፋፈል ነበረ። 14 አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ፤ ለእግዚአብሔርም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ። 15 በዚያም ወራት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጭመቂያን የሚረግጡትን፥ ነዶም የሚከምሩትን፥ የወይኑን ጠጅና የወይኑን ዘለላ፤ በለሱንም፥ ልዩ ልዩም ዓይነት ሸክም በአህዮች ላይ የሚጭኑትን፥ በሰንበትም ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያስገቡትን አየሁ፤ ገበያም ባደረጉበት ቀን አስመሰከርሁባቸው። 16 ደግሞም በእርስዋ የተቀመጡ ነበሩ፤ እነርሱም ዓሣዎችን፥ ልዩ ልዩም ዓይነት ሸቀጥ አምጥተው በሰንበት ቀን በኢየሩሳሌም ለይሁዳ ልጆች ይሸጡ ነበር። 17 ከይሁዳም አለቆችና ታላላቆች ጋር ተከራከርሁና እንዲህ አልኋቸው፥ “ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድን ነው? የሰንበትንስ ቀን ታረክሳላችሁን? 18 አባቶቻችሁ እንደዚህ አድርገው አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ በእኛና በዚች ከተማ ላይ አምጥቶ አልነበረምን? እናንተስ ሰንበትን በማርከሳችሁ በእስራኤል ላይ መዓትን ትጨምራላችሁ?” 19 ከዚህ በኋላ ሰንበት ከመግባቱ በፊት በኢየሩሳሌም በሮች ድንግዝግዝታ በሆነ ጊዜ በሮችዋ እንዲዘጉ፥ ሰንበትም እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ። በሰንበትም ቀን ሸክም እንዳይገባ ከብላቴኖች በዐያሌዎቹ በሮችዋን አስጠበቅሁ። 20 ሁሉም አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ከኢየሩሳሌም ውጭ አድረው ገበያ አድርገው ነበር። 21 እኔም አስመሰከርሁባቸውና፥ “ከቅጥሩ ውጭ ለምን ታድራላችሁ? እንደ ገና ብታደርጉት እጆችን አነሣባችኋለሁ” አልኋቸው። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ በሰንበት ቀን እንደ ገና አልመጡም። 22 ሌዋውያኑንም ራሳቸውን እንዲያነጹ፥ መጥተውም በሮቹን እንዲጠብቁ፥ የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ ነገርኋቸው። “አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ራራልኝ” አልሁ። 23 ደግሞም በዚያ ወራት የአዛጦንንና የአሞንን፥ የሞዓብንም ሴቶች ያገቡትን አይሁድ አየሁ። 24 ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ በአዛጦን ቋንቋ ይናገሩ ነበር፤ በሌሎች ሕዝብ ቋንቋ የሚናገሩም ነበሩ፤ በአይሁድም ቋንቋ መናገር አያውቁም ነበር። 25 እነርሱንም ተቈጣኋቸው፤ ረገምኋቸውም፤ ከእነርሱም ዐያሌዎቹን መታሁ፤ ጠጕራቸውንም ነጨሁ፤ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው፥ “ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ። 26 የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በዚህ ነገር ኀጢአት አድርጎ የለምን? በብዙ አሕዛብም መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፤ በአምላኩም ዘንድ የተወደደ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ አንግሦት ነበር፤ እርሱንም እንኳ እንግዶች ሴቶች አሳቱት። 27 እንዲሁ እንግዲህ ይህን ሁሉ ታላቅ ክፋት ስትሠሩ፥ እንግዶችንም ሴቶች በማግባት አምላካችንን ስትበድሉ አንስማባችሁ።” 28 ከዋነኛውም ካህን ከኤልያሴብ ልጅ ከዮዳሔ ልጆች አንዱ ለሐሮናዊው ለሰንባላጥ አማች ነበረ፤ ከእኔም ዘንድ አባረርሁት። 29 “አምላኬ ሆይ፥ ክህነትን የክህነትንና የሌዋውያንንም ቃል ኪዳን ስላፈረሱ አስባቸው።” 30 ከእንግዳ ነገርም ሁሉ አነጻኋቸው፤ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም ለእያንዳንዳቸው በየሰሞናቸው፥ 31 በየጊዜውም ዕንጨት ለሚሸከሙ ሰዎች ቍርባን፥ ለበኵራቱም ሥርዐት አደረግሁ። “አምላካችን ሆይ፥ በመልካም አስበኝ።” |