ኢዮብ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢዮብ የተወለደበትን ቀን እንደ ረገመ 1 ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፈተ፥ የተወለደባትንም ቀን ረገመ። 2 እንዲህም አለ፦ 3 “ያች የተወለድሁባት ቀን ትጥፋ፥ ያችም፦ ወንድ ልጅ ነው ያሉባት ሌሊት። 4 ያች ቀን ጨለማ ትሁን፤ እግዚአብሔር ከላይ አይመልከታት፥ ብርሃንም አይብራባት። 5 ጨለማና የሞት ጥላ ያግኙአት፤ ጭጋግም ይምጣባት፤ 6 ያች ቀንም የተረገመች ትሁን። ያችም ሌሊት ጨለማ ይምጣባት፤ በዓመቱ ቀኖች መካከል አትኑር፤ በወሮች ቀኖች ውስጥም ገብታ አትቈጠር። 7 ለዚያም ሌሊት ጭንቅ ይሁን፥ እልልታ ወይም ደስታ አይግባባት። 8 ነገር ግን ሌዋታንን ለመግደል የተዘጋጀ ያችን ቀን የሚረግም ይርገማት። 9 የዚያ ሌሊት ኮከቦች ይጨልሙ፤ ሌሊቱም በጨለማ ይኑር፤ ወደ ብርሃንም አይምጣ፤ የንጋት ኮከብም ሲወጣ አይይ፤ 10 የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥ መከራውንም ከዐይኔ አልሰወረምና። 11 በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም? ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ወዲያውኑ ስለ ምን አልጠፋሁም? 12 ጕልበቶች ስለ ምን ደገፉኝ? ጡትስ ስለ ምን ጠባሁ? 13 አሁንም ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፤ አንቀላፍቼም ባረፍሁ ነበር፤ 14 በሰይፋቸው ከከበሩ ከምድር ነገሥታትና መካሮች ጋር፥ 15 ወይም ወርቅን ካበዙ፥ ቤታቸውንም ብር ከሞሉ አለቆች ጋር፥ 16 ወይም ከእናቱ ማኅፀን እንደ ወጣ ጭንጋፍ፥ ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር። 17 ኃጥኣን በዚያ በቍጣው መቅሠፍት ይቃጠላሉ፤ በዚያም በሥጋቸው የተጨነቁት ያርፋሉ። 18 በዚያም የጥንት ዘመን ሰዎች በአንድነት፥ የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም። 19 ታናሹና ታላቁ በዚያ አሉ፤ ጌታውን ያገለገለ ባሪያም በዚያ አለ። 20 በመራራነት ላሉት ብርሃን፥ በነፍስ ለተጨነቁትም ሕይወት፥ 21 የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ፥ ሞትን ለሚመኙ ለማያገኙትም፥ 22 ባገኙትም ጊዜ ደስ ለሚላቸው፥ ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ? 23 ሞት ለሰው ዕረፍቱ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ከለከለው። 24 ከአዝመራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥ ስለ ደረሰብኝም አስፈሪ ነገር ሁልጊዜ አለቅሳለሁ። 25 የተጠራጠርሁት ነገር መጥቶብኛልና፥ ያሰብሁትም ደርሶብኛል። 26 ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ ፀጥታም አላገኘሁም፥ አላረፍሁም። ነገር ግን መከራ ደረሰችብኝ።” |