ሐዋርያት ሥራ 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ፊስጦስ ስለ መምጣቱና ስለ አይሁድ ልመና 1 ፊስጦስም ወደ ቂሣርያ ደርሶ ሦስት ቀን ሰነበተ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2 ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሎችም ከበቡት፤ የጳውሎስንም ነገር ነገሩት። 3 ልኮም ወደ ኢየሩሳሌም አደባባይ እንዲያስመጣውና እንዲሰጣቸው ለመኑት፤ እነርሱ ግን ወደዚያ ሄደው በመንገድ ሸምቀው ሊገድሉት ፈልገው ነበር። 4 ፊስጦስም ጳውሎስን በቂሣርያ እንደሚጠብቁት፥ እርሱም ራሱ ወደዚያው በቶሎ እንደሚሄድ መለሰላቸው። 5 አይሁድንም፥ “ከመካከላችሁ የሚችሉ ካሉ ከከሰሳችሁት ከዚያ ሰው ጋር እንዲከራከሩ ከእኔ ጋር ይውረዱ” አላቸው። 6 ስምንት ወይም ዐሥር ቀን በእነርሱ ዘንድ ከሰነበተ በኋላ ወደ ቂሣርያ ሄደ፤ በማግሥቱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ። 7 ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱ አይሁድ ከብበውት ቆሙ፤ ሊረቱ በማይችሉበትም ብዙና ከባድ ክስ ከሰሱት። 8 ጳውሎስም ሲመልስ፥ “በአይሁድ ሕግ ላይ ቢሆን፥ በቤተ መቅደስም ላይ ቢሆን፥ በቄሣር ላይም ቢሆን አንዳች የበደልሁት የለም” አለ። 9 ፊስጦስ ግን አይሁድ እንዲያመሰግኑት ወዶ ጳውሎስን፥ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር በዚያ ከእኔ ዘንድ ልትከራከር ትሻለህን?” አለው። 10 ጳውሎስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ ወደ ቄሣር ዙፋን ችሎት እቀርባለሁ፤ ፍርዴም በዚያ ሊታይልኝ ይገባል፤ በአይሁድም ላይ የበደልሁት በደል እንደሌለኝ ከሰው ሁሉ ይልቅ አንተ ራስህ ታውቃለህ። 11 ከበደልሁ ወይም ለሞት የሚያበቃኝ የሠራሁት ክፉ ሥራ ካለ ሞት አይፈረድብኝ አልልም፤ ነገር ግን እነዚህ በደል የሌለብኝን በከንቱ የሚከስሱኝ ከሆነ፥ ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጠኝ ለማን ይቻለዋል? እኔ ወደ ቄሣር ይግባኝ ብያለሁ።” 12 ከዚህም በኋላ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ፥ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ካልህ ወደ ቄሣር ትሄዳለህ” አለው። ጳውሎስ በአግሪጳና በበርኒቄ ፊት ስለ መቅረቡ 13 ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት። 14 በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው፥ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ። 15 በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ። 16 እኔም፦ ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም፥ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው። 17 ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ፥ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ። 18 የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ፥ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም። 19 ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው፥ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ 20 ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት። 21 ጳውሎስ ግን እንቢ ብሎ፥ እንዲድን ወደ ቄሣር ይግባኝ አለ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቄሣር እስክልከው ድረስ እንዲጠብቁት አዘዝሁ።” 22 አግሪጳም ፊስጦስን፥ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወዳለሁ” አለው፤ ፊስጦስም፥ “እንግዲያስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው። 23 በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ። 24 ፊስጦስም እንዲህ አለ፥ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ፥ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ። 25 እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ፥ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ። 26 ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም። ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት። 27 የበደሉ ደብዳቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል።” |