2 ዜና መዋዕል 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የንግሥተ ሳባ ጕዞ ወደ ኢየሩሳሌም ( 1ነገ. 10፥1-13 ) 1 የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቱና ብዙ ወርቅ፥ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤ ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሰሎሞንም ያልፈታው ነገር አልነበረም። 3 የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፤ 4 የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም ሥርዐት፥ አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ አለባበሳቸውንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ተደነቀች። 5 ንጉሡንም አለችው፥ “ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በሀገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 6 እኔ ግን መጥቼ በዐይኔ እስካየሁ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም፤ እነሆ፥ የጥበብህን ታላቅነት እኩሌታ አልነገሩኝም፤ በሀገሬ ከሰማሁትም ዝና ይልቅ ጨመርህልኝ። 7 እነዚህ ሰዎችህ ምስጉኖች ናቸው፤ በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙና ጥበብህን የሚሰሙ እነዚህ አገልጋዮችህም ምስጉኖች ናቸው። 8 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደህ አምላክህ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ አምላክህ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘለዓለም ያጸናቸው ዘንድ ወድዶአቸዋልና ስለዚህ ፍርድንና ጽድቅን ታደርግ ዘንድ በላያቸው አነገሠህ።” 9 ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፥ እጅግም ብዙ ሽቱ፥ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ ሽቱ ከቶ አልነበረም። 10 የኪራም አገልጋዮችና የሰሎሞን አገልጋዮችም ከሴፌር ለሰሎሞን ወርቅ አመጡ፤ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍም ደግሞ አመጡ። 11 ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት ደርብ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም ነበር። 12 እርስዋም ለንጉሡ ለሰሎሞን ካመጣችው የበለጠ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የወደደችውን ሁሉ፥ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከአገልጋዮችዋ ጋር ወደ ሀገርዋ ሄደች። የንጉሥ ሰሎሞን ሀብት ብዛት ( 1ነገ. 10፥14-25 ) 13 በየዓመቱም ወደ ሰሎሞን የሚመጣ የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። 14 ነጋድራሶችና ነጋዴዎች ከሚያመጡት ሌላ የዓረብ ነገሥታት ሁሉ፥ የምድሩም ሹሞች ወደ ንጉሡ ሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡ ነበር 15 ንጉሡም ሰሎሞን በጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በየአንዳንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው የጠራ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። 16 ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በየአንዳንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። 17 ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 18 ወደ ዙፋኑም የሚያስሄዱ፥ በወርቅ የተለበጡ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በዚህና በዚያ በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። 19 በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 20 ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ የወርቅ ነበረ፤ የሊባኖስ ዱር በተባለውም ቤቱ የሚገለገልበት ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ ነበረ፤ በሰሎሞንም ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር። 21 ለንጉሡም ከኪራም አገልጋዮች ጋር ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር፥ የዝሆንም ጥርስና ዝንጀሮ ይዘው ይመጡ ነበር። 22 ንጉሡም ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ በባለጠግነትና በጥበብ በለጠ። 23 የምድርም ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ሊያዩ ይመኙ ነበር። 24 ከእነርሱም እያንዳንዱ ገጸ በረከቱን፥ የወርቅንና የብርን ዕቃ፥ ልብስንና የጦር መሣሪያን፥ ሽቱውንም፥ ፈረሶችንና በቅሎዎችን እየያዘ በየዓመቱ ያመጣ ነበር። 25 ሰሎሞንም ለሰረገሎች አራት ሺህ እንስት ፈረሶችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎችም ከተሞች፥ ከንጉሡ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 26 ከኤፍራጥስም ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ዳርቻ ድረስ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ነገሠ። 27 ንጉሡም ወርቁንና ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ፥ የዝግባውንም እንጨት በቆላ እንደሚበቅል ሾላ ብዛት አደረገው። 28 ለሰሎሞንም ፈረሶች ከግብፅና ከየሀገሩ ሁሉ ይመጡለት ነበር። 29 የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአኪያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በኢዩሔል ራእይ የተጻፈ አይደለምን? 30 ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31 ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |