1 ነገሥት 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሰሎሞን ሹሞች 1 ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር። 2 የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፥ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፤ 3 ጸሓፊዎቹም የሱባ ልጆች ኤልያብና አኪያ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ነበረ። 4 የዮዳሄም ልጅ በንያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤ 5 የናታንም ልጅ ኦርኒያ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዘባት የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤ 6 አኪያልም የቤት አዛዥ፥ ኤልያቅም የቤት አዛዦች አለቃ ነበረ፥ የሳፋን ልጅ ኤልያፍም የቤተ ሰብ ሐላፊ፥ የአዶን ልጅ አዶኒራምም ግብር አስገባሪ ነበረ። 7 ሰሎሞንም ለንጉሡና ለቤተሰቡ ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ ዐሥራ ሁለት ሹሞችን ሾመ። ከዓመቱ ውስጥ እያንዳንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር። 8 ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው ሀገር በኤፍሬም የሖር ልጅ ቢዖር፥ 9 በማኪስና በሰአልቢን፥ በቤት ሳሚስና በኤሎንቤትሐናን የዴቀር ልጅ፥ 10 በአራቦት፥ በሶኮትና በኦፌር ሀገር ሁሉ የሔሴድ ልጅ ነበረ፤ 11 በዶር ሀገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ ነበረ፤ ለእርሱም የሰሎሞን ልጅ ጣፈትም ሚስቱ ነበረች፤ 12 ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤ 13 በሬማት ዘገለዓድ የጌቤር ልጅ ነበረ፤ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤ ለእርሱም ደግሞ በባሳን፥ በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወርወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤ 14 በማሃናይም የሳዶ ልጅ አሒናዳብ ነበረ፤ 15 በንፍታሌምም አኪማኦስ ነበረ፤ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባሴማትን አግብቶ ነበር፤ 16 በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና ነበረ፤ 17 በይሳኮርም የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ ነበረ፤ 18 በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ ነበረ፤ 19 በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ ሀገር፥ በጋድ ሀገር፥ የአዴ ልጅ ጌቤር ነበረ፤ በይሁዳም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ። 20 ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ ይበሉና ይጠጡም፥ ደስም ይላቸው ነበር። 21 ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብፅ ምድር ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤማውያን ሀገር ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፤ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር። 22 ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ቆሮስ መልካም ዱቄትና ስድሳ ቆሮስ መናኛ ዱቄት፤ 23 ከዋሊያና ከሚዳቋ፥ ከበረሃ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር ዐሥር ፍሪዳዎች፥ ሃያም የተሰማሩ በሬዎች፥ አንድ መቶም በጎች ነበረ። 24 ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ፥ ከወንዙም ወዲህ ባለው ሀገር ሁሉ ላይ ከቲላሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር። 25 በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዳቸው ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልለው ይቀመጡ ነበር። 26 ለሰሎሞንም ሰረገላ የሚስቡ አርባ ሺህ ፈረሶች፥ ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት። 27 እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጐድሉም ነበር። 28 እያንዳንዱም እንደ ደንቡ የንጉሡን ሰረገላዎች ለሚስቡ ለፈረሶችና ለሰጋር በቅሎዎች ገብስና ገለባ፥ እንዲሁም ዕቃዎችን ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር። 29 እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብንና ማስተዋልን፥ በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው። 30 የሰሎሞንም ጥበብ ከቀደሙ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብፅ ጥበብ ሁሉ በዛ። 31 ከሰዎችም ሁሉ ይልቅ ብልህ ነበረ፤ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከአውናንና ከከልቀድ፥ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። 32 ሰሎሞንም ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ መሐልዩም አንድ ሺህ አምስት ነበረ። 33 ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ አሽክት ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ስለ ተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። 34 ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡን ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር። |