1 ነገሥት 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮርብዓምም መሥዋዕት ይሠዋ ዘንድ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር። 2 የእግዚአብሔርም ሰው በመሠዊያው ላይ፥ “መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፤ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል” ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጠራ። 3 በዚያም ቀን፦ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ “እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በውስጡም ያለው ስብ ይፈስሳል” ብሎ ምልክት ሰጠ። 4 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኢዮርብዓም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የተናገረውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ንጉሡ፥ “ያዙት” ብሎ እጁን ከመሠዊያው ላይ አነሣ። ከዚህም በኋላ በእርሱ ላይ የዘረጋት እጁ ደረቀች፤ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። 5 የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ በውስጡም ያለው ስብ ፈሰሰ። 6 ንጉሡም ኢዮርብዓም የእግዚአብሔርን ሰው፥ “አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፤ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ” አለው፥ የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች። እንደ ቀድሞም ሆነች። 7 ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፥ “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ ምሳም ብላ፥ ስጦታም እሰጥሃለሁ” አለው። 8 የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን፥ “የቤትህን እኩሌታ እንኳን ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፤ በዚህም ስፍራ እንጀራን አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም፤ 9 እንጀራም አትብላ፤ ውኃም አትጠጣ፤ በመጣህበት መንገድም አትመለስ ሲል እግዚአብሔር በቃሉ አዝዞኛልና” አለው። 10 በሌላም መንገድ ሄደ፤ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም። የቤቴሉ ሽማግሌ ነቢይ 11 በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ይኖር ነበር፤ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያች ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ ሁሉ ነገሩት፤ ደግሞም ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት፤ አባታቸውም ተቈጣቸው። 12 አባታቸውም፥ “በየትኛው መንገድ ሄደ?” አላቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አመለከቱት። 13 ልጆቹንም፥ “አህያዬን ጫኑልኝ” አላቸው፥ አህያውንም ጫኑለት ተቀመጠበትም። 14 የእግዚአብሔርንም ሰው ተከትሎት ሄደ፤ ከዛፍ በታችም ተቀምጦ አገኘውና፥ “ከይሁዳ የመጣህ የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” አለው። እርሱም፥ “አዎ፥ እኔ ነኝ” አለ። 15 እርሱም፥ “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ እንጀራም ብላ” አለው። 16 እርሱም፥ “ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም፤ 17 በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፤ በመጣህበት መንገድም አትመለስ ብሎ እግዚአብሔር በቃሉ አዝዞኛልና” አለው። 18 እርሱም፥ “እኔ ደግሞ እንዳንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም፦ እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ” አለው። ዋሽቶም ተናገረው። 19 መለሰውም፥ በቤቱም እንጀራ በላ፤ ውኃም ጠጣ። 20 በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤ 21 ከይሁዳም የመጣውን የእግዚአብሔርን ሰው እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእግዚአብሔር ቃል ላይ አምፀሃልና፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥ 22 ተመልሰህም፦ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይገባም።” 23 እንጀራም ከበላ፥ ውኃም ከጠጣ በኋላ ለተመለሰው ነቢይ አህያውን ጫኑለት። 24 ተነሥቶም ሄደ፤ በመንገዱም ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋድሞ ነበር፤ አህያውም በእርሱ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ደግሞ በሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር። 25 እነሆም፥ መንገድ አላፊ ሰዎች ሬሳውን በመንገዱ ወድቆ፥ አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆሞ አዩ፤ ገብተውም ሽማግሌው ነቢይ ይኖርበት በነበረው ከተማ አወሩ። 26 ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ያን ሰምቶ፥ “በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያመፀ ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው” አለ። 27 ልጆቹንም፥ “አህያዬን ጫኑልኝ” አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት። 28 ሄዶም፥ ሬሳው በመንገድ ወድቆ፥ በሬሳውም አጠገብ አህያውና አንበሳው ቆመው፥ አንበሳውም ሬሳውን ሳይበላው፥ አህያውንም ሳይሰብረው አገኘ። 29 ነቢዩም የእግዚአብሔርን ሰው ሬሳ አነሣ፤ በአህያውም ላይ ጫነው፤ ነቢዩም በራሱ መቃብር ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው አመጣው፤ 30 ዋይ ዋይ፥ ወንድሜ ሆይ፥ እያሉም አለቀሱለት። 31 ከቀበሩትም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፥ “በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼ ከአጥንቶቹ ጋር ይድኑ ዘንድ አጥንቶቼን በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤ 32 በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉት በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የተናገረው ነገር በእውነት ይደርሳልና።” 33 ከዚህም በኋላ ኢዮርብዓም ከክፋቱ አልተመለሰም፤ ነገር ግን ለኮረብታዎቹ መስገጃዎች አብልጦ ከሕዝብ ሁሉ የጣዖት ካህናትን ሾመ፤ የሚወድደውንም ሁሉ ይቀድስ ነበር፤ እርሱም ለኮረብቶቹ መስገጃዎች ካህን ይሆን ነበር። 34 ይህም ነገር ከገጸ ምድር ለመፍረስና ለመጥፋት በኢዮርብዓም ቤት ላይ ኀጢአት ሆነ። |