Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሰው አእምሮ ውሱንነት 1 ስሙ ዑርኤል የተባለው ወደ እኔ የተላከው መልአክ መለሰልኝ። 2 “የልዑልን የጌትነቱን ምክር ታገኝ ዘንድ ልቡናህ ማድነቅን አደነቀን?” አለኝ። 3 “አዎ ጌታዬ፥” አልሁት፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ሦስቱን መንገዶች አሳይህ ዘንድ፥ ሦስቱንም ምሳሌዎች በፊትህ አኖር ዘንድ ተላክሁ፥ 4 ከእነዚህም አንዲቱን የተረጐምህልኝ እንደ ሆነ እኔም ታውቅ ዘንድ የምትወዳትን ይህችን መንገድ እነግርሃለሁ፤ ይህ ክፉ ልቡናም ስለምን እንደ ሆነ አስተምርሃለሁ።” 5 እኔም አልሁት፥ “አቤቱ ተናገር” እርሱም አለኝ፥ “እሳቱን በሚዛን መዝን፤ ነፋሱንም በመስፈሪያ ስፈር፤ ያለፈችውንም ቀን ጥራት።” 6 እኔም መልሼ እንዲህ አልሁት፥ “ስለዚህ ነገር እኔን እንደ ጠየቅኸኝ ይህን ነገር ማድረግ የሚችል የተፈጠረ ሰው ማን ነው?” 7 እርሱም አለኝ፥ “በባሕር ውስጥ ምን ያህል ቤቶች አሉ? ወይም በጥልቁ ውስጥ ምን ያህል ምንጮች አሉ? ወይም በሰማያት ላይ ምን ያህል መንገድ አለ? ወይም የሲኦል መንገድ በየት ነው? ወይም የገነት መንገድ በየት ነው? ብዬ ጠይቄህስ ቢሆን፥ 8 ወደ ጥልቁ አልወረድሁም፤ ወደ ሲኦልም ፈጽሜ አልወረድሁም፤ ወደ ሰማይም አልወጣሁም ባልኸኝ ነበር። 9 አሁን ግን ስለ ነፋስና ስለ እሳት፥ ስላለፈችውም ቀን እንጂ ይህን አልጠየቅሁህም፤ እነሆ፥ ልታውቀው አትችልም፤ ስለ እነዚህም የመለስህልኝ የለም። 10 በአንተ ዘንድ ያለውን ማወቅ ያልቻልህ፥ 11 የልዑልን የመንገዱን ሥርዐት እንዴት ማወቅ ትችላለህ? የልዑል መንገዱ ፍጻሜ በሌለው ተወስኗልና፥ የምትፈርስ፥ የምትበሰብስ አንተ የማይፈርስ፥ የማይበሰብስ የልዑልን መንገድ ማወቅ አትችልም።” 12 ይህንም በሰማሁ ጊዜ በግንባሬ ወደቅሁ፤ “ተፈጥረን በኀጢአት ከምንኖርና መከራን ከምንቀበል ባልተፈጠርን በተሻለን ነበር፤ መከራ እንድንቀበልም አናውቅም” አልሁት። የዛፎችና የባሕር ምሳሌ 13 መልሶም እንዲህ አለኝ፥ “ዛፍና የዱር እንጨቶች ሄደው ምክርን ተማከሩ። 14 ከፊታችን እናርቃት ዘንድ ኑ ሄደን ባሕርን እንውጋት፤ ለዛፍነታችንም ሌላ ሀገር እናቅና” አሉ። 15 እንደዚሁም የባሕር ማዕበላት ምክርን መከሩ፤ “ለማዕበልነታችን በዚያ ሌላ ሀገር እንድናቀና በምድረ በዳ ያለ ዛፍን እንወጋው ዘንድ ኑ እንዝመት” አሉ። 16 የዛፎች ምክር ከንቱ ሆነ፤ እሳት ወጥታ በልታቸዋለችና። 17 እንዲሁም የባሕር ማዕበላት ምክር ከንቱ ሆነ፤ አሸዋው ገድቦ ከልሎአቸዋልና። 18 “ፍርድ የምታውቅ ከሆነ ከእነዚህ ማንን እውነተኛ፥ ማንንስ ሐሰተኛ ታደርጋለህ?” አለኝ። 19 መልሼም እንዲህ አልሁ፥ “ሁለቱ ከንቱን ዐሰቡ፤ የብስ ለዛፍ፥ ባሕርም ማዕበልን ትሸከም ዘንድ ተሰጥታለችና።” 20 እርሱም መልሶ እንዲህ አለኝ፦“ መልካም ፈረድህ፤ እንዲሁ ለራስህ ለምን አትፈርድም? 21 የብስ ለዛፍ፥ ባሕርም ለማዕበልዋ እንደ ተሰጠች እንዲሁም በምድር የሚኖሩ ሰዎች በምድር ያለውን ማወቅ ይችላሉ እንጂ በሰማያትና ከሰማያት በላይ ያለውን አይደለም።” የዘመኑ ፍጻሜ 22 መልሼም እንዲህ አልሁት፥ “አቤቱ እጠይቅሃለሁ፤ እንግዲያው እናስብ ዘንድ ልብ ለምን ተሰጠን? 23 እኔ ግን የልዑልን መንገድ እጠይቅ ዘንድ አልወደድሁም፤ ሁልጊዜ በእኛ ላይ ስለሚያልፈው እንጂ፤ እስራኤል በውርደት ለአሕዛብ፥ የወደድኸውም ሕዝብ ለኀጢአተኞች ሕዝብ ተሰጥቶአልና። የአባቶቻችንም ኦሪት ጠፍታለችና፤ በውስጧም የተጻፈው ቃል ኪዳን የለምና። 24 ከዓለም እንደ አንበጣ እናልፋለን፤ ሕይወታችንም እንደ ጢስ ነው፤ ምሕረትንም ለማግኘት የተገባን አይደለንም። 25 ነገር ግን በእኛ ስለ ተጠራ ስለ ቅዱስ ስሙ ምን እናደርጋለን? ስለዚህ ነገር ጠየቅሁህ።” 26 እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “በሕይወት ካለህ ታየዋለህ፤ በሕይወት ብትኖርም በጊዜው ታውቀዋለህ፤ ዓለም ያልፍ ዘንድ ይቸኩላልና። 27 ዓለም የጻድቃንን ተስፋ ማስቀረት አይችልምና፥ ይህ ዓለም ጭንቅን የተሞላ ነውና፥ ደዌንም የተሞላ ነውና። 28 ስለእርሷ የጠየቅኸኝ ክፋት ተዘርታለችና፥ መከርዋም አልደረሰምና። 29 በውስጡም የተዘራው ካልታጨደና ካልተነሣ ክፋት የተዘራችበት ቦታው አይወገድም። 30 በመጀመሪያ ክፉ የዘር ቅንጣት በአዳም ልቡና ተዘርቶ ነበርና፥ የኀጢአት ፍሬም ተወልዷልና እስከ ዛሬም ድረስ ደርሷልና፥ መከሩም እስኪደርስ ድረስ ይወለዳል፤ 31 አንተ ራስህ እስኪ አስበው! የክፉ ዘር ቅንጣት ቢዘራ ይህን ያህል የኀጢአት ፍሬ ተወለደች። 32 የመልካም ዘር ቅንጣት ግን ብትዘራ ቍጥር የሌለውን መልካም ፍሬን እንዴት ባፈራች ነበር!!” 33 መልሼም እንዲህ አልሁት፥ “ደገኛው እስከ መቼ ይሆናል? የዚህ ዓለም ዘመኑ ክፉም፥ ጥቂትም ነውና።” 34 መልሶም እንዲህ አለኝ፥ “ከልዑል ይልቅ አንተ እጅግ የምትቸኩል አይደለህም፤ አንተስ ስለ ራስህ ትቸኩላለህ፤ ልዑል ግን ስለ ብዙዎች ይቸኩላል። 35 ስለዚህ የጻድቃን ነፍሳት በማደሪያቸው ሁነው ጠየቁ፤ በዚህ እስከ መቼ ድረስ እንኖራለን? የዋጋችንስ መከር መቼ ይደርሳል?” አሉ። 36 መልአኩ ኢይሩማኤልም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፥ “እንደ እናንተ ያሉት ጻድቃን ቍጥራቸው በተፈጸመ ጊዜ ነው። 37 ይህ ዓለም በሚዛን ተመዝኗልና፥ ባሕሩንም በመስፈሪያ ሰፍሮታልና፤ የተሰጠውም መስፈርት እስኪፈጸም ድረስ ዝም ይላል፤ አይነቃምም።” 38 እኔም መልሼ እንዲህ አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ እነሆ፥ እኛ ሁላችን ኀጢአትን የተመላን ነን፤ 39 ምናልባት የጻድቃን የዋጋቸው መከር በእኛ ምክንያት ይከለከላልን? ወይስ በዚህ ዓለም ስለሚኖሩት ሰዎች ኀጢአት ነው?” 40 እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ዘጠኝ ወር ከተፈጸመ በኋላ በማኅፀንዋ ያለውን ልጅዋን ማስቀረት ይቻላት እንደ ሆነ ሄደህ የፀነሰች ሴትን ጠይቃት።” 41 እኔም መልሼ አልሁት፥ “አቤቱ አትችልም፥” እርሱም አለኝ፥ “ሲኦልና የጻድቃን ነፍሳት ማደሪያዎችም እንዲሁ ናቸው። 42 ማኅፀን በምጥ ጊዜ ለመውለድ እንደምትቸኩል ምድርም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተቀበሩባት ሰዎችን ትሰጥ ዘንድ ትቸኩላለች። 43 ያንጊዜም ታውቅ ዘንድ የምትወድደውን ነገር እነግርሃለሁ፥” ምን ያህል ዘመን እንደ ቀረ 44 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “በፊትህ ባለሟልነትን ካገኘሁ፥ ልጠይቅም እንዲቻለኝ ካደረግኸኝ ይኽን ንገረኝ። 45 ይመጣ ዘንድ ያለው ዘመን ባለፈው ዘመን ልክ ነውን? ወይስ ያለፈው ዘመን ይበዛል? 46 ያለፈውን አውቀዋለሁና፥ የሚመጣውን ግን አላውቀውምና።” 47 እርሱም አለኝ፥ “በቀኝ በኩል ባንድ ወገን ሁነህ ቁም፤ የምሳሌውንም ትርጓሜ አሳይሀለሁ።” 48 እኔም ቆምሁ፤ እነሆም ምድጃ በፊቴ እየነደደ ሲሄድ አየሁ፤ ከዚህም በኋላ እሳቱ በሄደ ጊዜ እነሆ ጢሱ ቀረ። 49 ከእርሱም በኋላ ውኃን የተመላች ደመና በፊቴ ሄደች፤ ታላቅና ብዙ የሆነ ዝናምንም ታዘንማለች፤ ታላቁ ዝናምም ካለፈ በኋላ ካፊያው ቀረ። 50 እርሱም አለኝ፥ “እንግዲህ እስኪ አንተ ዐስበው፤ ከካፊያው ዝናሙ፥ ከጢሱ እሳቱ እንደሚበዛ፥ እንደዚሁም ያለፈው መስፈርት ይበዛል፤ ነገር ግን ካፊያውም ጢሱም ይቀራል። 51 “እስከ እነዚያ ዘመኖች ድረስ እኖራለሁን? እንጃ! በእነዚያስ ወራቶች ምን ይደረጋል?” ብዬ ማለድሁት። 52 እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ስለ ጠየቅኸኝ ምልክትስ ከብዙ በጥቂቱ መንገር ይቻለኛል፤ ስለ ሕይወትህ ግን እነግርህ ዘንድ አልተላክሁም፤ እኔም አላውቀውም። |