Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ምሳሌ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ብልኅ ልጅ የአባቱን ምክር ይቀበላል፤ ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም።

2 ደጋግ ሰዎች የመልካም አነጋገራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ የአታላዮች ምኞት ግን የግፍ ሥራ ለመፈጸም ነው።

3 ተጠንቅቆ የሚናገር ሕይወቱን ይጠብቃል። ግዴለሽ ተናጋሪ ግን ጥፋት ይደርስበታል።

4 ሰነፍ አንድ ነገር ለማግኘት አጥብቆ ይመኛል፤ ይሁን እንጂ አያገኝም፤ ትጉህ ሠራተኛ ግን የሚፈልገውን ሁሉ ያገኛል።

5 ደጋግ ሰዎች ሐሰትን ይጠላሉ፤ የክፉዎች ሰዎች ንግግር ግን አሳፋሪና አስነዋሪ ነው።

6 ደጋግ ሰዎች ደግነታቸው ይጠብቃቸዋል፤ ኃጢአተኞችን ግን ኃጢአታቸው ያጠፋቸዋል።

7 አንዳንድ ሰዎች ምንም ሳይኖራቸው ሀብታም መስለው ለመታየት ይጥራሉ፤ ሌሎች ደግሞ ብዙ ሀብት እያላቸው፥ ምንም ሀብት እንደሌላቸው መስለው ይኖራሉ።

8 ሀብታም በገንዘብ ሕይወቱን ለማዳን ይጣጣራል፤ ድኻ ግን የሚወሰድበት ሀብት ስለሌለው አይጨነቅም።

9 የጻድቃን ብርሃን ያንጸባርቃል፤ የኃጢአተኞች መብራት ግን ይጠፋል።

10 ትዕቢት ጠብን ያመጣል፤ ምክርን መጠየቅ ግን ብልኅነት ነው።

11 ያለ ድካም በቀላሉ የተገኘ ሀብት ወዲያው ይጠፋል፤ ተግቶ በመሥራት የተገኘ ሀብት ግን እየበዛ ይሄዳል።

12 ተስፋ ሲዘገይ ልብን ያሳዝናል፤ የተመኙት ነገር ሲፈጸም ግን ደስ ያሰኛል።

13 መልካም ምክርን የሚንቅ ችግር ይደርስበታል፤ ትእዛዝን የሚያከብር ግን ዋጋ ያገኝበታል።

14 የጠቢባን ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ሕይወትህ በአደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳ እንድታመልጥ ይረዳሃል።

15 አስተዋይ መሆን ያስከብራል፤ ከዳተኛነት ግን ወደ ጥፋት ያደርሳል።

16 አስተዋይ ሰዎች ለሚሠሩት ሥራ አስቀድመው ዕቅድ ያወጣሉ፤ ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን አላዋቂነታቸውን ይገልጣሉ።

17 ክፉ መልእክተኛ ችግርን ያመጣል፤ ታማኝ መልእክተኛ ግን ሰላምን ያስገኛል።

18 ትምህርት የማይወድ ሰው፥ ድኽነትና ውርደት ይገጥመዋል፤ ተግሣጽን የሚቀበል ግን ይከበራል።

19 የተመኙትን ነገር ማግኘት እጅግ ደስ ያሰኛል፤ ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን ከክፉ ነገር መራቅ አይፈልጉም።

20 ከጥበበኞች የሚወዳጅ ጥበበኛ ይሆናል። ማስተዋል ከጐደላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ የሚሆን ግን ይጐዳል።

21 ኃጢአተኞችን በሄዱበት ስፍራ ሁሉ መከራ ይከተላቸዋል፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ።

22 ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ የሚተላለፍ ሀብት ያገኛል፤ የኃጢአተኞችን ሀብት ግን ቅን ሰዎች ይወርሱታል።

23 የድኻ እርሻ የተትረፈረፈ ምርትን ሊያስገኝ ይችል ይሆናል። ከፍርድ መጓደል የተነሣ ግን ይጠፋል።

24 ልጁን የማይቀጣ አይወደውም ማለት ነው፤ ልጁን የሚወድ ግን ቀጥቶ ያሳድገዋል።

25 እውነተኞች ሊበሉ የሚፈልጉትን ያኽል ያገኛሉ። ኃጢአተኞች ግን ዘወትር ይራባሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos