Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የእግዚአብሔር ክብር ከኢየሩሳሌም መለየት

1 እኔም አየሁ፥ እነሆ ከኪሩቤል ራስ በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ፥ ዙፋን የሚመስል ነገር ታየ።

2 በፍታም የለበሰውን ሰው እንዲህ አለው፦ በመንኰራኵሮች መካከል ከኪሩብ በታች ግባ፥ ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ በከተማይቱም ላይ በትናት ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ።

3 ሰውዬው ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ በደቡብ በኩል ቆመው ነበር፥ ደመናውም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላው።

4 የጌታ ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መግቢያ ላይ ቆመ፥ ቤቱም በደመናው ተሞላ፥ አደባባዩም በጌታ የክብር ብርሃን ተሞላ።

5 ሁሉን የሚችል አምላክ ሲናገር እንደሚያሰማው ዓይነት ድምፅ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጭው አደባባይ ድረስ ተሰማ።

6 በፍታ የለበሰውን ሰው ሲያዘው፦ ከኪሩቤል መካከል ከመንኰራኵሮች መካከል እሳት ውሰድ አለው፥ እርሱም ገብቶ በአንድ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ።

7 ከኪሩቤል መካከል አንድ ኪሩብ እጁን በኪሩቤል መካከል ወዳለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ ወሰደ፥ በፍታ በለበሰው ሰው እጅም አኖረው፥ እርሱም ይዞ ወጣ።

8 ኪሩቤልም ከክንፎቻቸው በታች የሰው እጅ የሚመስል ታየ።

9 እኔም አየሁ፥ እነሆ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፥ አንድ መንኰራኵር በአንድ ኪሩብ፥ አንድ መንኰራኵር በአንድ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ የቢረሌ ድንጋይ ይመስል ነበር።

10 የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፥ በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበር።

11 ሲሄዱም በአራቱም ጎናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር፥ ራስ ወደዞረበት ስፍራ ወደዚያ ይከተሉ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር።

12 መላ አካላቸው ሁሉ፥ ጀርባቸው፥ እጃቸው፥ ክንፋቸው፥ መንኰራኵሮቹም፥ የአራቱም መንኰራኵሮች፥ ዙሪያቸው በሙሉ በዐይኖች ተሞልተው ነበር።

13 መንኰራኵሮችም እኔ እየሰማሁ “የሚሽከረከሩ መንኰራኵሮች” ተብለው ተጠሩ።

14 እያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት፥ አንደኛው ፊት የኪሩብ ፊት፥ ሁለተኛው ፊት የሰው ፊት፥ ሦስተኛው ፊት የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም ፊት የንስር ፊት ነበረ።

15 ኪሩቤልም ተነሡ፥ እነዚህ በኮቦር ወንዝ ያየኋቸው ሕያዋን ናቸው።

16 ኪሩቤልም ሲሄዱ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር፥ ኪሩቤል ከምድር ለመነሣት ክንፎቻቸውን ሲዘረጉ መንኰራኵሮቹም ከአጠገባቸው አይለዩም ነበር።

17 የሕያዋኑ መንፈስ በመንኰራኵሮች ውስጥ ስለ ነበረ እነዚህ ሲቆሙ እነዚያም ይቆሙ ነበር፥ እነዚህ ሲነሱ እነዚያም ከእነርሱ ጋር ይነሱ ነበር።

18 የጌታ ክብር ከቤቱ መግቢያ ወጥቶ ከኪሩቤል በላይ ቆመ።

19 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ እኔም እያየሁ ከምድር ተነሡ፥ ሲወጡም መንኰራኵሮች በአጠገባቸው ነበሩ፥ በጌታ ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ቆሙ፥ የእስራኤል አምላክ ክብርም በላያቸው ላይ ነበረ።

20 እነዚህ በኮበር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየኋቸው ሕያዋን ናቸው፥ እኔም ኪሩቤል እንደ ነበሩ አስተዋልሁ።

21 እያንዳንዱ አራት አራት ፊት፥ እያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት፥ ከክንፎቻቸው ሥርም የሰው እጅ የሚመስል ነገር ነበረ።

22 ፊቶቻቸውም በኮበር ወንዝ ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፥ እነርሱና መልካቸውም እንዲሁ ነበረ፥ እያንዳንዱ ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos