1 በቴቁሔ በላም ጠባቂዎች መካከል የነበረ አሞጽ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከሆነበት ከሁለት ዓመት በፊት ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል ይህ ነው። 2 እንዲህም አለ፥ “እግዚአብሔር ከጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፤ ከኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ የእረኞችም ማሰማሪያዎች ያለቅሳሉ፤ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።” ስለ ቂር3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የገለዓድን ነፍሰ ጡሮች በብረት መጋዝ ሰንጥቀዋቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 4 በአዛሄል ቤት ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የወልደ አዴርንም መሠረቶች ትበላለች። 5 የደማስቆንም ቍልፎች እሰብራለሁ፤ በአዎን ሸለቆ የሚኖሩትንም ሰዎች አጠፋለሁ፤ የካራን ሰዎች ወገኖችንም እቈራርጣለሁ፤ የሶርያ ሕዝብም ወደ ቂር ይማረካሉ፤” ይላል እግዚአብሔር። ስለ ፍልስጥኤም6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በኤዶምያስ ይዘጉባቸው ዘንድ የሰሎሞንን ምርኮ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 7 በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ መሠረቶችዋንም ትበላለች። 8 የአዛጦን ነዋሪዎችን አጠፋለሁ፤ የአስቀሎናም ሕዝብ ይጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፤ ከፍልስጥኤማውያን የቀሩትም ይጠፋሉ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ስለ ጢሮስ9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የሰሎሞን ምርኮኞችን በኤዶምያስ ዘግተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኀጢአት አልመለስላቸውም። 10 በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን አሰድዳለሁ፤ መሠረቶችዋንም ትበላለች።” ስለ ኤዶም11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦“ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ በምድር ላይም ማኅፀንን አርክሶአልና፥ የሚዘልፈውንና የሚያስደነግጠውን በርብሮአልና፥ መዓቱንም ለዘለዓለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 12 በቴማን ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የቅጥርዋንም መሠረቶች ትበላለች።” ስለ አሞን13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ዳርቻቸውን ያሰፉ ዘንድ የገለዓድን ነፍሰ ጡሮች ቀድደዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአሞን ልጆች ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 14 በራባ ቅጥር ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ በጦርነት ቀን በጩኸት መሠረቶችዋን ትበላለች፤ በፍጻሜዋም ቀን ትናወጣለች። 15 ንጉሦቻቸውን፥ አለቆቻቸውንና ካህኖቻቸውን በአንድነት ይማርኳቸዋል፥” ይላል እግዚአብሔር። |