La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


መዝሙር 79 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም
መዝሙር 79

ስለ ሕዝብ ሰላም የሚቀርብ ጸሎት

1 አምላክ ሆይ! አሕዛብ ወደ ምድርህ መጡ፤ ቤተ መቅደስህን አረከሱ፤ ኢየሩሳሌምንም አፈራረሱአት።

2 የሕዝብህን ሬሳ ለሰማይ ወፎችና የታማኞችህን ሥጋ ለአራዊት ምግብ አድርገው ሰጡ።

3 ደማቸውንም እንደ ውሃ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ አፈሰሱ፤ የሞቱትንም የሚቀብር አንድ ሰው እንኳ አልነበረም።

4 ለጐረቤቶቻችን መዘባበቻ፥ በዙሪያችን ላሉ መሳቂያና መሳለቂያ ሆነናል።

5 እግዚአብሔር ሆይ! በእኛ ላይ የምትቈጣው እስከ መቼ ድረስ ነው? ቅናትህ እንደ እሳት ሲነድ ይኖራልን?

6 ቊጣህን አንተን በአምላክነትህ ወደማያውቁና ወደ አንተ ወደማይጸልዩ ሕዝቦችና መንግሥታት ላይ መልስ።

7 ይህንንም የምታደርገው እነርሱ ሕዝቦችህን ስለ ገደሉና ርስታቸውን ስለ አወደሙ ነው።

8 እኛ በጣም ስለ ተዋረድን በአባቶቻችን ኃጢአት ምክንያት አትቅጣን ፈጥነህም ምሕረት አድርግልን።

9 አዳኛችን አምላክ ሆይ! እርዳን፤ ስለ ራስህ ክብር ስትል ተቤዠን፤ ኃጢአታችንንም ይቅር በልልን።

10 ለምን አሕዛብ “አምላካቸው የት አለ?” ብለው ይጠይቁ? የፈሰሰውን የአገልጋዮችህን ደም እንደምትበቀል በፊታችን ለአሕዛብ አሳውቅ።

11 የእስረኞች መቃተት ወደ አንተ እንዲደርስ አድርግ፤ ሞት የተፈረደባቸውንም በታላቁ ኀይልህ አድናቸው።

12 ጌታ ሆይ! ጐረቤቶቻችን በአንተ ላይ ስለ ተዘባበቱ በሰባት እጥፍ ተበቀላቸው።

13 በዚያን ጊዜ የመንጋህ በጎች የሆንን ሕዝቦችህ ለዘለዓለም እናመሰግንሃለን፤ ለተከታዩ ትውልድ ሁሉ ምስጋናህን እንናገራለን።

Mostrar Biblia Interlineal

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia