መዝሙር 80 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ እስራኤል መንግሥት እንደገና መቋቋም የቀረበ ጸሎት 1 የእስራኤል እረኛ፥ የዮሴፍን ልጆች እንደ መንጋ የምትመራ አምላክ ሆይ! በኪሩቤል ላይ ባለው ዙፋንህ ተቀምጠህ፥ ጸሎታችንን አድምጥ፤ ብርሃንህም ይብራ። 2 ለኤፍሬም፥ ለብንያምና ለምናሴ ራስህን ግለጥ፤ ኀይልህን አነሣሥተህ መጥተህ አድነን። 3 አምላክ ሆይ! ከተሰደድንበት መልሰን፤ እንድንድን ምሕረትህን አሳየን! 4 የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! የሕዝብህን ጸሎት ባለመቀበል ቊጣህን የምትገልጠው እስከ መቼ ነው? 5 ሐዘንን እንደ ምግብ፥ እንባንም እንደ መጠጥ በብዛት ሰጠሃቸው። 6 በዙሪያችን ያሉ መንግሥታት መሬታችንን ለመውሰድ እርስ በእርሳቸው እንዲዋጉ አደረግህ፤ ጠላቶቻችን ሁሉ ይሳለቁብናል። 7 የሠራዊት አምላክ ሆይ! ከተሰደድንበት መልሰን! እንድንድን ምሕረትህን አሳየን። 8 የወይን ሐረግን ከግብጽ አመጣህ፤ ሌሎች ሕዝቦችን አስወግደህ በምድራቸው እርስዋን ተከልክ። 9 የምታድግበትን ቦታ መነጠርህላት፤ ሥሮችዋ በመሬት ውስጥ ጠልቀው መሠረት ያዙ፤ በምድሩም ላይ ተንሰራፋች። 10 ጥላዋ ተራራዎችን የቅርንጫፎችዋም ጥላ የሊባኖስ ዛፎችን ሸፈነ። 11 ቅርንጫፎችዋን እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕርና እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ዘረጋች። 12 ታዲያ፥ በዙሪያዋ የነበረውን አጥር ስለምን አፈረስህ? እነሆ፥ ከዚህ የተነሣ በአጠገብዋ የሚያልፍ ሰው ሁሉ ፍሬዋን ይቀጥፋል። 13 የዱር እርያዎች ይረጋግጡአታል፤ የበረሓ አራዊትም ይመገቡአታል። 14 የሠራዊት አምላክ ሆይ! ፊትህን ወደ እኛ መልስ! ከሰማይ ወደ እኛ ወደ ታች ተመልከት፤ እይም፤ ይህን የወይን ግንድህን ጠብቅ! 15 ይህችን አንተ የተከልካትን ተንከባክበህም ያሳደግኻትን የወይን ግንድ ጠብቃት! 16 ጠላቶች ቈራርጠው በእሳት አቃጥለዋታል፤ በቊጣህ ተመልከታቸው፤ አጥፋቸውም! 17 በቀኝህ ያለውንና ለክብርህ ብርቱ ያደረግኸውን ጠብቀህ በሰላም አኑረው። 18 ከእንግዲህ ወዲህ ከአንተ አንርቅም፤ በሕይወት ጠብቀን፤ እኛም እናመሰግንሃለን። 19 የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ከተሰደድንበት መልሰን፤ እንድንድን ምሕረትህን አሳየን። |