La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


መዝሙር 143 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም
መዝሙር 143

የእግዚአብሔርን ዕርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት

1 እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ! ለምሕረት የማደርገውን ልመና አድምጥ! በታማኝነትህና በእውነተኛነትህ ለጸሎቴ መልስ ስጠኝ!

2 በአንተ ፊት ማንም ጻድቅ ሰው ስለሌለ እኔን አገልጋይህን ለፍርድ አታቅርበኝ።

3 ጠላቴ በማሳደድ ተከታተለኝ፤ በጨለማ ውስጥም አስሮ አጐሳቈለኝ፤ ከብዙ ዘመናት በፊት እንደ ሞቱ ሰዎች ሆኜአለሁ።

4 ከዚህም የተነሣ መንፈሴ በውስጤ ዛለብኝ፤ ልቤም ተስፋ ቈረጠ።

5 ከብዙ ጊዜ በፊት የነበረውን አስታውሳለሁ፤ ሥራዎችህንም ሁሉ አሰላስላለሁ፤ የእጅህን ሥራዎች ሁሉ አስተውላለሁ።

6 እጆቼን ለጸሎት ወደ አንተ እዘረጋለሁ፤ ደረቅ ምድር ውሃ እንደሚያስፈልገው እንዲሁም ነፍሴ አንተን ተጠማች።

7 እግዚአብሔር ሆይ! መንፈሴ ስለ ዛለብኝ ፈጥነህ መልስ ስጠኝ! ፊትህን ከእኔ አትሰውርብኝ! አለበለዚያ ወደ ጥልቁ ጒድጓድ እንደሚወርዱት ሰዎች እሆናለሁ።

8 የምተማመነው በአንተ ስለ ሆነ በየጠዋቱ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ ሕይወቴን በዐደራ ለአንተ ስለ ሰጠሁ የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ።

9 እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ስለ ተማጠንኩ ከጠላቶቼ አድነኝ።

10 አንተ አምላኬ ነህ፤ ፈቃድህን እንዳደርግ አስተምረኝ፤ በመልካም ቸርነትህ በደኅና መንገድ ምራኝ።

11 እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ክብርህ ሕይወቴን ጠብቅ፤ በእውነተኛነትህም ከችግሬ ሁሉ ነጻ አውጣኝ።

12 ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥልኝ፤ ጠላቶቼን አጥፋቸው፤ እኔ አገልጋይህ ስለ ሆንኩ ጥቃት የሚያደርሱብኝን ሁሉ ደምስሳቸው።

Mostrar Biblia Interlineal

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia