መዝሙር 142 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔርን ርዳታ ለማግኘት የሚቀርብ ጸሎት 1 ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ ምሕረት እንዲያደርግልኝ እለምነዋለሁ። 2 አቤቱታዬን ሁሉ በፊቱ አቀርባለሁ፤ ችግሬንም ሁሉ እነግረዋለሁ። 3 ተስፋ ለመቊረጥ ጥቂት በቀረኝ ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ ያውቃል፤ ጠላቶቼ በምሄድበት መንገድ ላይ ወጥመድ ዘረጉብኝ። 4 በዙሪያዬ ስመለከት መሸሸጊያ የሚሆነኝ አጣሁ፤ አንድም እንኳ የሚረዳኝ ሰው አልነበረም፤ የሚጠብቀኝና የሚጠነቀቅልኝም አልነበረም። 5 እግዚአብሔር ሆይ! እንድትረዳኝ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ! ጠባቂዬ አንተ ነህ፤ በሕያዋን ምድር ዕድል ፈንታዬ አንተ ነህ። 6 በጣም ተስፋ የቈረጥሁ ስለ ሆነ እንድትረዳኝ ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤ እጅግ በርትተውብኛልና ከጠላቶቼ አድነኝ። 7 አመሰግንህ ዘንድ ከእስራቴ አውጣኝ፤ ለእኔ ያደረግኸውን ያንተን የቸርነት ሥራ በሚያዩበት ጊዜ ሕዝብህ በዙሪያዬ ይሰበሰባሉ። |