Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 144 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የድል አድራጊነት መዝሙር

1 መጠጊያዬ እግዚአብሔር ይመስገን! ለሰልፍ ያሠለጥነኛል፤ ለጦርነትም ያዘጋጀኛል።

2 እግዚአብሔር ጠባቂዬና መከታዬ ነው፤ መጠለያዬና አዳኜ ነው፤ በእርሱ ተማምኜ በሰላም እኖራለሁ፤ እርሱ አሕዛብን ከእግሬ በታች አድርጎ ያስገዛልኛል።

3 እግዚአብሔር ሆይ! ይህን ያኽል የምትንከባከበው ሰው ምንድን ነው? ይህን ያኽልስ የምታስብለት የሰው ልጅ ምንድን ነው?

4 ሰው እንደ ነፋስ ሽውታ ነው፤ ዘመኑም እንደ ጥላ የሚያልፍ ነው።

5 እግዚአብሔር ሆይ! ሰማይን ሰንጥቀህ ውረድ፤ ተራራዎችን ዳስስ፤ እነርሱም ይጢሱ።

6 የመብረቅ ብልጭታን ልከህ ጠላቶችህን በትናቸው፤ ፍላጻዎችህንም በመወርወር አሳዳቸው።

7 እጅህን ከላይ ስደድ፤ ከጥልቅ ውሃ ውስጥ ስበህ አውጣኝ፤ ታደገኝም፤ ከባዕዳን ኀይል አድነኝ።

8 እነርሱ ከቶ እውነት አይናገሩም፤ ቀኝ እጃቸውን አንሥተው የሚምሉት በሐሰት ነው።

9 አምላክ ሆይ! አዲስ መዝሙር እቀኝልሃለሁ፤ ዐሥር አውታር ያለው በገናም በመደርደር እዘምርልሃለሁ።

10 አንተ ለነገሥታት ድልን ታጐናጽፋለህ፤ አገልጋይህን ዳዊትንም ከስለታም ሰይፍ ትታደገዋለህ።

11 ከባዕዳን ጠላቶች እጅ ታድገህ አድነኝ፤ አፋቸው ሐሰትን ይናገራል፤ ቀኝ እጃቸውም ለሐሰት መሐላ ይነሣል።

12 ወንዶች ልጆቻችን በወጣትነታቸው ጊዜ እንደ አዲስ ተክል የሚያድጉና የሚጠነክሩ ይሁኑ፤ ሴቶች ልጆቻችን ለቤተ መንግሥት ማእዘኖች ውበት እንደሚሰጡ፥ ተቀርጸው ቀጥ እንዳሉ ምሰሶች ይሁኑ።

13 ጐተራዎቻችን በልዩ ልዩ ዐይነት እህል የተሞሉ ይሁኑ፤ በመስኮቻችን ላይ የተሰማሩት በጎች በሺህ የሚቈጠሩ ግልገሎችን እየወለዱ ይብዙ።

14 ከብቶቻችን የሰቡ ይሁኑ፤ ሳይጨነግፉም በመርባት ይብዙ፤ በመንገዶቻችን የሐዘን ጩኸት ከቶ አይሰማ።

15 እንደዚህ የሚሆንለት ሕዝብ የተባረከ ነው! እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ የተባረከ ነው!

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos