1 ወዳጅ ከሆንክ በኋላ ጠላት አትሁን፤ መጥፎ ስም እፍረትን፥ ጥላቻን ያመጣል፥ በባለ ሁለት ምላሱ ኃጢአተኛ ላይ እንደሚደርሰው ሁሉ። 2 በስሜት አክናፍ አትብረር፤ ኃይልህ እንደ ኮርማ ይበታተናልና። 3 ቅጠሎችህን ትበላለህ፥ ፍሬዎችህንም ታጠፋለህ፥ አንተም የደረቀ እንጨት ትሆናለህ። 4 መጥፎ ባሕርይ ባለቤቱን ያጠፋል፤ የጠላቶቹ መሳቂያ ያደርገዋል። ወዳጅነት 5 መልካም አነጋገር ወዳጆችን ለማፍራት ያስችላል፤ ትሕትናን የተላበሰ አንደበት ወዳጃዊ መልስን ያስገኛል፤ አማካሪህ ግን ከሺ አንድ ይሁን። 6 ሰላምታ የሚሰጡህ ብዙዎች ይሁኑ፤ አማካሪህ ግን ከሺህ አንድ ይሁን። 7 ወዳጅ ስትይዝ ፈትነው፤ ቶሎ ብለህ አትመነው። 8 ወዳጅነቱ ለጊዜው የሆነና፤ በመከራ ቀን ወዳጅ ሆኖ የማይገኝ ሰው አለ። 9 ሌላኛው ዓይነት ወዳጅ፥ ከአንተ ጋር አይሰማማም፤ ይባስ ብሎም ጸባችሁ እንዲታወቅ ያደርጋል። 10 ሦስተኛው ዓይነት ወዳጅ፤ በአንድ ገበታ አብሮህ ይቀርባል፤ በመከራ ጊዜም ከአንተ ጋር አይቆምም። 11 አንተን በተመቸህ ጊዜ አንተን ይሆናል፤ አገልጋዮችህንም ለማዘዝ አይፈራም። 12 መከራ በወደቀብህ ጊዜ ከአንተ ይርቃል፤ ከመንገድህም ይሸሻል። 13 ከጠላቶችህ ራቅ፤ ከወዳጆችህ ተጠንቀቅ። 14 ታማኝ ወዳጅ ጽኑ መከታ ነው፤ እሱን ያገኘ ታላቅ ሃብትን አግኝቷል። 15 ታማኝ ወዳጅ ዋጋ አይገኝለትም፤ ውድነቱም አይሰፈርም። 16 ታማኝ ወዳጅ የሕይወት ቅመም ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ያገኙታል። 17 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እውነተኛ ወዳጆችን ያፈራል፤ ወዳጁም እርሱን ይመስላልና። ጥበብን መከተል18 ልጄ ሆይ ከወጣትነትህ ጀምረህ ጥበብን ምረጥ፤ ፀጉርህ እስኪሸብት ድረስ ጥበብን ፈልጋት። 19 እንደ አራሽ፥ እንደ ዘሪ ገበሬ፥ እርሷን ኮትኩታት፤ መልካም መኸሯንም ተጠባበቅ፥ እርግጥ ነው ለማረስና ለመዝራት ትደክማለህ፤ ነገር ግን በቶሎ ፍሬዋን ትበላለህ። 20 ላልተገሩ ሰዎች ጥበብ ምንኛ ትከብዳለች፤ አርቀው የማያዩ ከእርሷ ጋር አይዘልቁም። 21 እንደ ከባድ ቋጥኝ ትከብደዋለች፤ እርሱም እርግፍ አድርጎ ይተዋታል። 22 ጥበብ በስምዋ ታማኝ ነች፤ ሁሉም የሚያገኛትም አይደለችም፤ 23 ልጄ ሆይ ምክሬን ተቀበል፥ አታቃለውም፤ 24 እግሮችህን በእግር ብረቷ፥ አንገትህን በአንገትዋ አስገባ። 25 እርሷን ለመሸከም ትከሻህን ዝቅ አድርግ፤ በእግር ብረቷም አትበሳጭ። 26 በፍጹም ልብህ ወደሷ ሂድ፤ መንገዷን በፍጹም ኃይልህ ጠብቅ። 27 ፈልጋት፥ ተከተላት፤ እርሷም እራሷን ትገልጽልሀለች፤ አንዴ ከያዝካት አትልቀቃት። 28 በመጨረሻ ዕረፍት በሷ ታገኛለህ፤ ስለ አንተ ደስታ ትሆንልሀለች። 29 እግረ ሙቋ የማይበገር መከታ ይሆንሃል፤ አንገት ጌጥዋም የከበረ ሃብል ይሆናል። 30 ቀንበርዋ የወርቅ ጌጥ ይሆንልሃል፤ ማሰሪያዎችም የከፋይ ጥብጣብ ይሆኑልሃል። 31 እንደ ክቡር ካባ ትደርባታለህ፤ እንደ ደስታ አክሊልም ትቀዳጃታለህ። 32 ልጄ ሆይ ከፈለግህ ትምህርትን ታገኛለህ፤ በልብህም ከተጋህ ብልህ ትሆናለህ። 33 መስማትን ከወደድህ መማር ትችላለህ፤ ካዳመጥህ ጥበበኛ ትሆናለህ፤ 34 በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ተገኝ፤ ብልህም ሰው ካለ ከእርሱ አትራቅ። 35 ከእግዚአብሔር የመጣውን ንግግር በፈቃደኝነት አድምጥ፤ አንድም የጥበብ ምሳሌ እንዳያመልጥህ ንቃ። 36 አስተዋይ ሰው ካገኘህ በማለዳ ጎብኘው፤ እግርህ የበሩን ደፍ ይመላለስ። 37 የእግዚአብሔርን ትእዛዞች አስብ፤ ትእዛዞቹን ያለማቋረጥ አጥና፤ እሱ ራሱ ልብህን ያበረታልሃል፤ የምትሻውንም ጥበብ ታገኛለህ። |