La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


ሉቃስ 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
ሉቃስ 13

ንስሓ የማይገባ ሁሉ ይጠፋል

1 በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት።

2 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በእነዚህ የገሊላ ሰዎች ላይ ይህ የደረሰው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ሆኑ ይመስላችኋልን?”

3 “አይደለም”፤ እላችኋለሁ፥ “ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንዲሁ ትጠፋላችሁ።

4 ወይንስ በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤

5 ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።”

የማታፈራ የበለስ ዛፍ ምሳሌ

6 ይህንንም ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን አትክልቱ ቦታ የተተከለች በለስ ነበረችው፤ በእርሷም ፍሬ ፈልጎ ቢመጣ ምንም አላገኘም።

7 የወይን አትክልት ሠራተኛውንም ‘እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ፈልጌ ለሦስት ዓመት ብመላለስ ምንም አላገኘሁም፤ ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቁላለች?’ አለው።

8 እርሱ ግን መልሶ፥ ጌታ ሆይ! ዙሪያዋን እስክኰተኩትላትና ፍግ እስካፈስላት ድረስ ይህችን ዓመት ደግሞ ተዋት።

9 ወደፊትም ብታፈራ፥ መልካም ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ” አለው።

ኢየሱስ በሰንበት አንዲት ጎባጣ ሴት እንደ ፈወሰ

10 በሰንበት ቀንም ከምኵራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር።

11 እነሆም፥ ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ በሽተኛ ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ጎባጣ ነበረች፤ ቀጥ ብላ መቆምም በፍጹም አልተቻላትም።

12 ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት! ከበሽታሽ ተፈውሰሻል፤” አላት፤

13 እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።

14 የምኵራብ አለቃው ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን “ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይሆንም፤” አለ።

15 ጌታም መልሶ እናንተ ግብዞች! ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን?

16 ይህች ለዐሥራ ስምንት ዓመት ሰይጣን ያሠራት የአብርሃም ልጅ በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው።

17 ይህንንም ሲናገር የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ በእርሱም በተደረጉት ድንቅ ነገሮች ሁሉ ሕዝቡ በሙሉ ደስ አለው።

ስለ ሰናፍጭ ዘር እና ስለ እርሾ ምሳሌ
( ማቴ. 13፥31-33 ፤ ማር. 4፥30-32 )

18 እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ምንን ትመስላለች? በምንስ እመስላታለሁ?

19 ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤እርሷም አደገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ፤”።

20 ደግሞም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ?

21 አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች፤” አለ።

ስለ ጠባብዋ በር
( ማቴ. 7፥13-14 ፤ 21-23 )

22 ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር።

23 አንድ ሰውም “ጌታ ሆይ! የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦

24 “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ፥ አይችሉምም እላችኋለሁ።

25 ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም መልሶ ‘ከየት እንደ ሆናችሁ አላውቅም’ ይላችኋል።

26 በዚያን ጊዜም ‘በፊትህ በላን፤ ጠጣንም፤ በአደባባያችንም አስተማርህ፤’ ማለት ትጀምራላችሁ፤

27 እርሱም ‘እላችኋለሁ፥ ከየት እንደ ሆናችሁ አላወቅም፤ ዐመፀኞች በሙሉ፥ ከእኔ ራቁ፤’ ይላችኋል።

28 አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት እያያችሁ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

29 ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ።

30 እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፤ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”

ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን እንደ ወቀሰ
( ማቴ. 23፥37-39 )

31 በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዶች ቀርበው “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ውጣና ሂድ፤” አሉት።

32 እንዲህም አላቸው “ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ ‘እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን እፈጽማለሁ’ በሉአት።

33 ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊጠፋ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም መሄድ ያስፈልገኛል።

34 ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም! ነቢያትን የምትገድል፥ ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፤ እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።

35 እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል። በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።

Mostrar Biblia Interlineal