La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


2 ዜና መዋዕል 35 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
2 ዜና መዋዕል 35

የፋሲካ በዓል መከበሩ

1 ኢዮስያስም ለጌታ በኢየሩሳሌም ፋሲካን አከበረ፤ በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን መሥዋዕት አረዱ።

2 ካህናቱንም በየሥርዓታቸው አቆመ፥ በጌታም ቤት እንዲያገለግሉ አጸናቸው።

3 እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለጌታም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን ጌታንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤

4 የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፉት በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ራሳችሁን አዘጋጁ፤

5 እንደ ሕዝቡም እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶቻችሁ ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱ ለተከፋፈሉትም ለአባቶች ቤቶች ሌዋውያን ይኑሯቸው፤

6 ፋሲካውንም እረዱ፥ እናንተም ተቀደሱ፥ ጌታም በሙሴ አንደበት የተናገረውን ቃል እንዲያደርጉ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።”

7 ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም በሬዎች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ።

8 መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የጌታም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ።

9 የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ።

10 አገልግሎቱም በተዘጋጀ ጊዜ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ።

11 የፋሲካውንም መሥዋዕት አረዱ፥ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፥ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ።

12 በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለጌታ እንዲያቀርቡ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ።

13 የፋሲካውንም መሥዋዕት እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቁርባን በምንቸትና በሰታቴ በድስትም ቀቀሉ፥ ለሕዝቡም ሁሉ በፍጥነት አደረሱ።

14 ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ።

15 የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍም እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ የደጁም ጠባቂዎች በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው እንዲርቁ አያስፈልጋቸውም ነበር።

16 እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በጌታ መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ፋሲካውንም እንዲያከብሩ የጌታ አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ።

17 የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አከበሩ።

18 ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ ተከብሮ አያውቅም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳከበሩት ያለ ፋሲካ ያከበረ የለም።

19 ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ተከበረ።

ንጉሥ ኒካዑ ማሸነፍና ንጉሥ ኢዮሲያስ መሞቱ

20 ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ባሰናዳ ጊዜ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ሄደ።

21 ኒካዑም እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት፦ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ውግያ የማደርገው በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ ጌታም እንድቸኩል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው ጌታ እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ።”

22 ኢዮስያስ ግን ማንነቱን ሸሽጎ ለመዋጋት ወጣ እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በጌታም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ለመዋጋት መጣ።

23 ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም አገልጋዮቹን፦ “ክፉኛ ቆስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው።

24 አገልጋዮቹም ከሠረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሠረገላ ውስጥ አስቀመጡት፥ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፥ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ።

25 ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል።

26 የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በጌታም ሕግ እንደ ተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥

27 የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።

Mostrar Biblia Interlineal