ምሳሌ 21:1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እርሱም እንደ ቦይ ውሃ ደስ ወዳሠኘው ይመራዋል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በጌታ እጅ ነው፥ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እርሱንም እንደ ወራጅ ውሃ ወደ ፈቀደው ይመራዋል። የንጉሥንም አእምሮ ይቈጣጠራል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሽ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ይመልሳታል፥ በዚያም ትቈያለች። |
በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያ ዓመት፣ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤
“የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንድሠራለት አዝዞኛል።
እግዚአብሔር ደስ እንዲሰኙ ስላደረጋቸው የቂጣን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አከበሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ልብ ለውጦ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ቤት ሥራ እንዲያግዛቸው አድርጎ ነበር።
ጌታ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎት፣ ስምህን በመፍራት ደስ የሚሰኙትን የባሪያዎችህንም ጸሎት ጆሮህ ታድምጥ። በዚህ ሰው ፊት ሞገስን አድርገህለት ዛሬ ለባሪያህ መከናወንን ስጠው።” በዚያ ጊዜ እኔ የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበርሁ።
እንዲሁም ለንጉሡ ደን ጠባቂ ለአሳፍ፣ በቤተ መቅደሱ አጠገብ ላለው ግንብ በሮች፣ ለከተማዪቱ ቅጥርና እኔም ለምገባበት ቤት ሠረገላ የሚሆን ዕንጨት እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይጻፍልኝ፤” መልካሚቱ የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ ነበረችና ንጉሡም ፈቀደልኝ።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹ ደናግልም ሁሉ ይልቅ በርሱ ዘንድ ሞገስንና መወደድን አገኘች። ስለዚህ የእቴጌነት ዘውድ በራሷ ላይ ጫነላት፤ በአስጢንም ፈንታ ንግሥት አደረጋት።
እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤
የምድር ሕዝቦች ሁሉ፣ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይ ኀይላት፣ በምድርም ሕዝቦች ላይ፣ የወደደውን ያደርጋል፤ እጁን መከልከል የሚችል የለም፤ “ምን ታደርጋለህ?” ብሎ የሚጠይቀውም የለም።
ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብጽም ንጉሥ በፈርዖን ፊት ሞገስና ጥበብን አጐናጸፈው፤ ፈርዖንም በግብጽና በቤተ መንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው።
ስድስተኛውም መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸው የወንዙ ውሃ ደረቀ።