ዘኍል 18:8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያም እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፤ “ለእኔ በሚቀርበው መባ ላይ ኀላፊነትን የሰጠሁህ እኔው ራሴ ነኝ፤ እስራኤላውያን የሚያቀርቡልኝም የተቀደሰ መባ ሁሉ ለአንተና ለልጆችህ መደበኛ ድርሻችሁ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው፦ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን እንደ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባኔን ሁሉ ለአንተ እንድትጠብቀው ሰጥቼሃለሁ፤ ለአንተና ለልጆችህ የክህነትህ ድርሻ እንዲሆን ለአንተ የተገባህ አድርጌ ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፦ “ለእኔ የሚቀርበውን የማይቃጠለውን ልዩ መባ ሁሉ ለአንተ የሰጠሁህ መሆኑን አስታውስ፤ እርሱ ለዘለዓለም ለአንተና ለዘሮችህ ሁሉ ድርሻ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው፤ እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የለዩትን የመጀመሪያውን ቍርባኔን ሁሉ ትጠብቁ ዘንድ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ለአንተ እስክታረጅ፥ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ የዘለዓለም ሕግ እንዲሆን ሰጥቼሃለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው፦ እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን የማንሣት ቍርባኔን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ስለ መቀባትህ ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ። |
ካህናቱና ሌዋውያኑም ሙሉ ጊዜያቸውን ለእግዚአብሔር ሕግ አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጣቸው አዘዘ።
ትእዛዙ እንደ ወጣ እስራኤላውያን ወዲያውኑ የእህሉንና የአዲሱን ወይን ጠጅ፣ የዘይቱንና የማሩን እንዲሁም የዕርሻውን ፍሬ ሁሉ በኵራት በልግስና ሰጡ፤ ካላቸው ከማንኛውም ነገር ሁሉ ላይ እጅግ ብዙ የሆነ ዐሥራት አውጥተው አመጡ።
አሮንና ወንድ ልጆቹ ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ወይም በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ፣ በደል ፈጽመው እንዳይሞቱ እነዚህን መልበስ አለባቸው። “ለአሮንና ለትውልዶቹ ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።
በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅብዐ ዘይቱ ወስደህ በአሮንና በልብሶቹ ላይ እንዲሁም በወንዶች ልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ርጨው። ከዚያም እርሱና ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም ልብሶቻቸው የተቀደሱ ይሆናሉ።
ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የዘወትር የእስራኤላውያን ድርሻ የሚሆነው ይህ ነው፤ ከኅብረት መሥዋዕታቸው እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ነው።
“ ‘ከወንድሞቹ መካከል ተለይቶ በራሱ ላይ ዘይት የፈሰሰበትና የክህነት ልብስ እንዲለብስ የተቀባው ካህን የራስ ጠጕሩን አይንጭ፤ ወይም ልብሱን አይቅደድ።
ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋራ የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው።
ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’ ”
“አሮን ወይም ልጆቹ በተቀቡበት ዕለት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፦ የኢፍ አንድ ዐሥረኛው የላመ ዱቄት ግማሹን ለጧት፣ ግማሹን ለማታ የዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ያቅርቡት።
ከእያንዳንዱም ዐይነት አንዳንድ አንሥቶ ለእግዚአብሔር የተለየ ቍርባን በማድረግ ያቅርብ፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቱን ደም ለሚረጨው ካህን ይሰጥ።
ቀጥሎም ሙሴ በመቅቢያው ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት ወስዶ፣ በአሮንና በልብሱ እንዲሁም በአሮን ልጆችና በልብሳቸው ላይ ረጨ፤ በዚህም ሁኔታ አሮንንና ልብሱን፣ ልጆቹንና ልብሳቸውን ቀደሰ።
ለእኔ ከሚቀርብልኝ እጅግ ከተቀደሰው መባ ሁሉ፣ በእሳት የማይቃጠለው የራስህ ድርሻ ይሆናል፤ እጅግ የተቀደሰ አድርገው ከሚያመጡልኝ ስጦታ ከእህል ቍርባንም ሆነ ከኀጢአት ወይም ከበደል መሥዋዕት የሚነሣው ሁሉ የአንተና የልጆችህ ድርሻ ነው።
ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ።
ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ።
ሌዋውያን ካህናት፣ የሌዊ ነገድም ሁሉ ከእስራኤል ጋራ የመሬት ድርሻ ወይም ርስት አይኖራቸውም፤ ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መባ ይብሉ፤ ድርሻቸው ነውና።
ከዚያ በኋላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲህ በል፤ “በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት የተቀደሰውን ክፍል ከቤቴ አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም።
እናንተ ግን ከርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን የርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር፣ እውነተኛ የሆነውን እና ሐሰት ያልሆነው እናንተን እንደሚያስተምር፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ።