ዘኍል 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየሰፈሩ መንጻት 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ተላላፊ የቈዳ በሽታ ያለበትን ወይም ማንኛውም ዐይነት ፈሳሽ ከሰውነቱ የሚወጣውን ወይም ሬሳ በመንካቱ በሥርዐቱ መሠረት የረከሰውን ሰው ሁሉ ከሰፈር እንዲያስወጡ እስራኤላውያንን እዘዝ፤ 3 ወንድም ሆነ ሴት አስወጡ፤ እኔ በመካከላቸው የምኖርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈር አስወጧቸው።” 4 እስራኤላውያን ይህንኑ አደረጉ፤ ሰዎቹንም ከሰፈር አስወጧቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘውም መሠረት ፈጸሙ። የካሳ አከፋፈል 5 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ወንድም ሆነ ሴት በማናቸውም ረገድ ሌላውን ቢበድልና ከዚህም የተነሣ ለእግዚአብሔር ባይታመን በደለኛ ነው 7 በሠራው ኀጢአት ይናዘዝ፤ ስለ በደሉም ሙሉ ካሳ ይክፈል፤ የተመደበበትም ካሳ ላይ አንድ ዐምስተኛ በመጨመር በደል ላደረሰበት ሰው ይስጥ፤ 8 ነገር ግን ይህ ሰው ካሳውን የሚቀበልለት ዘመድ ከሌለው ካሳው ለእግዚአብሔር ስለሚሆን ማስተስረያ እንዲሆነው ከሚያቀርበው አውራ በግ ጋራ ለካህኑ ይስጥ። 9 እስራኤላውያን የሚያመጧቸው የተቀደሱ ስጦታዎች ሁሉ ለተቀባዩ ካህን ይሆናሉ፤ 10 የእያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ ስጦታ ለካህኑ ይሆናል፤ ለካህኑ የሚሰጠውም ሁሉ የራሱ ይሆናል።’ ” በአመንዝራነት ስለሚጠረጠሩ ሚስቶች 11 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘አንዲት ባለትዳር ሴት ወደ ሌላ ወንድ በማዘንበል ለባሏ ባትታመን፣ 13 ከሌላ ሰው ጋራ ብትተኛ፣ ይህም እጅ ከፍንጅ ባለመያዟ ምክንያት ይህ ከባሏ ቢደበቅ፣ የሚመሰክርባት ሰው ባይኖርና መርከሷም ባይገለጥ፣ 14 ባሏ የቅናት መንፈስ ዐድሮበት ቢጠረጥርና በርግጥም ጐድፋ ብትገኝ ወይም ባሏ የቅናት መንፈስ ዐድሮበት ቢጠረጥርና እርሷ ግን ጐድፋ ባትገኝ፣ 15 ወደ ካህኑ ይውሰዳት፤ ስለ እርሷም አንድ ኪሎ ገብስ ዱቄት ለቍርባን ይውሰድ፤ በላዩ ላይ ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት፤ ይህ ስለ ቅናት የቀረበ የእህል ቍርባን በደልን የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና። 16 “ ‘ካህኑ ሴትዮዋን ያመጣትና በእግዚአብሔር ፊት እንድትቆም ያደርጋታል፤ 17 ከዚያም ካህኑ የተቀደሰ ውሃ በሸክላ ዕቃ ቀድቶ በማደሪያው ድንኳን ካለው ወለል ጥቂት ዐፈር ቈንጥሮ በውሃው ውስጥ ይጨምራል። 18 ካህኑ ሴትዮዋን በእግዚአብሔር ፊት እንድትቆም ካደረገ በኋላ የጠጕሯን መሸፈኛ ይገልጣል፤ ስለ ቅናት የቀረበውን የመታሰቢያ ቍርባን በእጇ ያስይዛታል፤ ከዚያም ካህኑ ርግማን የሚያመጣውን መራራ ውሃ በእጁ ይይዛል። 19 ካህኑም ሴትዮዋን ያስምላታል፤ እንዲህም ይላታል፤ “ሌላ ወንድ ዐብሮሽ ካልተኛ፣ በትዳር ላይ ሆነሽ ወደ ርኩሰት ካላዘነበልሽ ይህ ርግማን የሚያመጣ መራራ ውሃ ጕዳት አያድርስብሽ፤ 20 ነገር ግን በትዳር ላይ እያለሽ ወደ ርኩሰት በማዘንበል ከባልሽ ሌላ ከወንድ ጋራ በመተኛት ከጐደፍሽ”፣ 21 እዚህ ላይ ካህኑ እንዲህ በማለት ሴትዮዋን በርግማን መሐላ ያስምላታል፤ “እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለለና ሆድሽን እያሳበጠ በሕዝብሽ መካከል ርግማንና መሐላ ያድርግብሽ፤ 22 ይህን ርግማን የሚያመጣ ውሃ በጠጣሽ ጊዜም ሆድሽን ያሳብጠው፤ ጭንሽን ያስልለው።” “ ‘ሴትዮዋም፣ “አሜን፤ አሜን” ትበል። 23 “ ‘ካህኑ እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ላይ ይጻፍ፤ በመራራውም ውሃ ይደምስሳቸው። 24 ርግማን የሚያመጣውንም ውሃ ሴትዮዋ እንድትጠጣ ያድርግ፤ ውሃውም ወደ ሰውነቷ ገብቶ የመረረ ሥቃይ ያስከትልባታል። 25 ካህኑ ለቅናት የቀረበውን የእህል ቍርባን ይቀበላት፤ በእግዚአብሔር ፊት ወዝውዞ ወደ መሠዊያው ያቅርበው። 26 ካህኑ የመታሰቢያ ቍርባን እንዲሆን ዕፍኝ የእህል ቍርባን ከዚያ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ከዚያም በኋላ ሴቲቱ ውሃውን እንድትጠጣ ያድርግ። 27 ራሷን በማጕደፍ ለባሏ ባትታመን፣ ርግማን የሚያመጣውን ውሃ እንድትጠጣ ሲደረግ ውሃው ወደ ሰውነቷ ገብቶ ክፉ ሥቃይ ያመጣባታል፤ ሆዷ ያብጣል፤ ጭኗ ይሰልላል፤ በሕዝቦቿም ዘንድ የተረገመች ትሆናለች። 28 ዳሩ ግን ሴትዮዋ ካልጐደፈችና ነውር ከሌለባት ከበደሉ ነጻ ትሆናለች፤ ልጆችም ትወልዳለች። 29 “ ‘እንግዲህ የቅናት ሕግ ይህ ነው፤ አንዲት ሴት በትዳር ላይ እያለች ወደ ሌላ ሄዳ ከረከሰች፣ 30 ወይም አንድ ሰው ሚስቱን ከመጠርጠሩ የተነሣ የቅናት መንፈስ ሲያድርበት በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፤ ካህኑም ሕጉ በሙሉ በሴቲቱ ላይ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ያድርግ። 31 ባልየውም ከበደል ንጹሕ ይሆናል፤ ሴትዮዋ ግን በበደሏ ምክንያት የሚመጣውን ፍዳ ትቀበላለች።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.