ሰቈቃወ 2:9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም በሮቿ ወደ ምድር ሰመጡ፤ የብረት መወርወሪያዎቻቸውን ሰባበረ፤ አጠፋቸውም፤ ንጉሧና መሳፍንቷ በአሕዛብ መካከል ተማርከው ተሰድደዋል፤ ሕጉ ከእንግዲህ አይኖርም፤ ነቢያቷም ከእንግዲህ፣ ከእግዚአብሔር ራእይ አያገኙም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ፤ ሰበረም፤ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፥ ነቢዮችዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የቅጽር በሮች ከመሬት በታች ተቀበሩ፤ መወርወሪያዎቻቸውም ተሰባብረው ወደቁ፤ ንጉሡና መሳፍንቱ አሁን በአሕዛብ መካከል በስደት ላይ ናቸው፤ የኦሪት ሕግ ትምህርት ከእንግዲህ ወዲህ አይሰጥም፤ ነቢያትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አይገለጥላቸውም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፤ መወርወሪያዎችዋም ተሰበሩ፤ ንጉሥዋና አለቃዋ በአሕዛብ መካከል አሉ፤ ሕግም የለም። ነቢያቷም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላዩም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ ሰበረም፥ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፥ ነቢያቶችዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም። |
እነርሱም፣ “በሕይወት ተርፈው ከምርኮ ወደ አገራቸው የተመለሱት ሰዎች በታላቅ መከራና ውርደት ላይ ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሷል፤ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ።
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤ በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ።
የባቢሎን ጦረኞች መዋጋት ትተዋል፤ በምሽጎቻቸው ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኀይላቸው ተሟጥጧል፤ እንደ ሴት ሆነዋል፤ በማደሪያዎቿም እሳት ተለኵሷል፤ የደጇም መወርወሪያ ተሰብሯል።
በመከራና በመረገጥ ብዛት ይሁዳ ተማርካ ሄደች፤ በሕዝቦችም መካከል ተቀመጠች፤ የምታርፍበትንም ስፍራ ዐጣች፤ በጭንቀቷ መካከል ሳለች፣ አሳዳጆቿ ሁሉ አገኟት።
ሰዎች “ሂዱ! እናንተ ርኩሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤ “ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤ ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣ በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣ “ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ።
መረቤን በርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል፤ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ነገር ግን እርሷን ሳያያት በዚያ ይሞታል።
ጥፋት በጥፋት ላይ፣ ወሬም በወሬ ላይ ይመጣል። ራእይን ከነቢይ ለማግኘት ይጥራሉ፤ የሕግ ትምህርት ከካህኑ፣ ምክርም ከሽማግሌው ዘንድ ይጠፋል።
የደማስቆን በሮች እሰባብራለሁ፤ በቤት ዔደን በትር የያዘውን፣ በአዌን ሸለቆ ያለውን ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርኮ ወደ ቂር ይሄዳል” ይላል እግዚአብሔር።
እግዚአብሔር አንተንና በላይህ ያነገሥኸውን ንጉሥ፣ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል፤ ከዚያም ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ።
እግዚአብሔር እናንተን በማበልጸግና ቍጥራችሁን በማብዛት ደስ እንደ ተሠኘ፣ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም ደስ ይለዋል፤ ልትወርሷት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።