ኤርምያስ 8:16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም የጠላት ፈረሶች ፉርፉርታ፣ ከዳን ይሰማል፤ በድንጉላ ፈረሶቻቸው ማሽካካት፣ መላዋ ምድር ተንቀጠቀጠች። ምድሪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ፣ ከተማዪቱንና በውስጧ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሊውጡ መጡ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “የፈረሶቻቸው ድምፅ ከዳን ተሰማ፤ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፤ መጡም ምድሪቱንና በእርሷም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ጠላቶቻችን እስከ ዳን ከተማ ደርሰዋል፤ ፈረሶቻቸው ሲያንኮራፉ ድምፃቸው ይሰማል፤ ሰንጋ ፈረሶቻቸውም ሲያሽካኩ ምድር ትናወጣለች፤ ጠላቶቻችን የመጡት ምንም ሳያስቀሩ ሕዝባችንንና ከተሞቻችንን እንዲሁም በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ ለማጥፋት ነው።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የፈረሶቹን የሩጫ ድምፅ ከዳን ሰማን፤ ከሠራዊቱ ፈረሶች ሩጫ ድምፅ የተነሣም ምድር በመላዋ ተንቀጠቀጠች፤ መጥተውም ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማዪቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የፈረሰኞቹ ድምጽ ከዳን ተሰማ፥ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፥ መጡም ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። |
ያዕቆብን አሟጥጠው ስለ በሉት፣ ፈጽመው ስለ ዋጡት፣ መኖሪያውንም ወና ስላደረጉ፣ በማያውቁህ ሕዝቦች፣ ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ፣ ቍጣህን አፍስስ።
“ ‘ነገር ግን አሟጥጠው የበሉህ ሁሉ እንደዚያው ይበላሉ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ለምርኮ ዐልፈው ይሰጣሉ፤ የሚዘርፉህ ይዘረፋሉ፤ የሚበዘብዙህም ሁሉ ይበዘበዛሉ።
አንበሳ ከደኑ ወጥቷል፤ ሕዝብንም የሚያጠፋ ተሰማርቷል፤ ምድርሽን ባዶ ሊያደርግ፣ ከስፍራው ወጥቷል። ከተሞችሽ ፈራርሰው ይወድቃሉ፤ ያለ ነዋሪም ይቀራሉ።
ከፈረስ ኮቴ ድምፅ፣ ከጠላት ሠረገላ ጩኸትና ከሠረገላው ሽክርክሪት ፍትጊያ ድምፅ የተነሣ፣ አባቶች ልጆቻቸውን ለመርዳት ወደ ኋላ መለስ አይሉም፤ እጃቸውም ስንኩል ይሆናል።
ሰብልህንና ምግብህን ጠራርገው ይበሉብሃል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን ይውጣሉ፤ በጎችህንና ከብቶችህን ይፈጃሉ፤ የወይን ተክሎችህንና የበለስ ዛፎችህን ያወድማሉ፤ የታመንህባቸውንም የተመሸጉ ከተሞች በሰይፍ ያጠፏቸዋል።
ቀስትና ጦር ይዘዋል፤ ጨካኞች ናቸው፤ ምሕረትም አያደርጉም፤ በፈረሳቸው እየጋለቡ ሲመጡ፣ ድምፃቸው እንደ ባሕር ሞገድ ይተምማል፤ ያስገመግማል። አንቺ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፤ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ተዋጊዎች ይመጡብሻል።
ሰው በዚያ መኖር እስከማይችል ድረስ፣ የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ ያቀደው ስለሚጸና፣ ምድር ትናወጣለች፤ በሥቃይም ትወራጫለች።
ቀስትና ጦር ይዘዋል፤ ጨካኞችና ምሕረት የለሽ ናቸው፤ ፈረሶቻቸውን ሲጋልቡ፣ ድምፃቸው እንደ ተናወጠ ባሕር ነው፤ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ለሰልፍ የታጠቁ ሆነው፣ ሊወጉሽ ይመጣሉ።”
ከዚያም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እንዲሁም በገለዓድ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወጡ፤ በምጽጳም በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ።