መዝሙር 24 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 24 የዳዊት መዝሙር። 1 ምድርና በርሷ ያለው ሁሉ፣ ዓለምና በውስጧ የሚኖር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤ 2 እርሱ በባሕሮች ላይ መሥርቷታልና፤ በውሆችም ላይ አጽንቷታል። 3 ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ሊወጣ ይችላል? በተቀደሰ ስፍራውስ ማን ይቆማል? 4 ንጹሕ እጅና ቅን ልብ ያለው፤ ነፍሱን ለሐሰት ነገር የማያስገዛ፤ በውሸት የማይምል። 5 እርሱ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ ጽድቅንም ከአዳኝ አምላኩ ይቀበላል። 6 እርሱን የሚፈልግ ትውልድ እንዲህ ነው፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፤ ፊትህን የሚፈልግ እንዲህ ያለ ነው። ሴላ 7 እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤ እናንተ የዘላለም በሮች፤ የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ! 8 ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው ብርቱና ኀያል፤ እግዚአብሔር ነው በውጊያ ኀያል። 9 እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤ እናንተ የዘላለም በሮች፤ የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ! 10 ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው። ሴላ |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.