ኤርምያስ 21:7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያ በኋላ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን፣ ከመቅሠፍት፣ በከተማው ከሰይፍና ከራብ የተረፈውንም ሕዝብ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆርና ሕይወታቸውን ለማጥፋት ለሚሹ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፤ አይራራላቸውም፤ አይምራቸውምም።’ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከዚህ በኋላ፥ ይላል ጌታ፥ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን፥ ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህችም ከተማ የቀሩትን፥ አገልጋዮቹንና ሕዝቡን በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፥ አይራራላቸውም፥ አይምራቸውም።’ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አንተና መኳንንትህ ከወረርሽኝ፥ ከጦርነትና ከራብ የሚተርፉትንም ሕዝብ በሙሉ በንጉሥ ናቡከደነፆርና ሊገድሉህ በሚፈልጉህ ጠላቶችህ እንድትማረኩ አደርጋለሁ፤ እርሱም ምሕረት ወይም ርኅራኄ በማሳየት አንድ ሰው እንኳ አይተውልህም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና አገልጋዮቹን፥ ከቸነፈርና ከሰይፍ፥ ከራብም በዚህች ከተማ የቀሩትን ሕዝቡንም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፤ አይራራላቸውም፤ አይምራቸውም።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከዚህ በኋላ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህች ከተማ የቀሩትንም ባሪዎቹንና ሕዝቡን በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፥ አያዝንላቸውም፥ አይራራላቸውም፥ አይምራቸውም። |
ሕዝቤን ተቈጥቼ ነበር፤ ርስቴን አርክሼው ነበር፤ አሳልፌ በእጅሽ ሰጠኋቸው፤ አንቺ ግን አልራራሽላቸውም፤ በዕድሜ በገፉት ላይ እንኳ፣ እጅግ ከባድ ቀንበር ጫንሽባቸው።
አንዱን ሰው ከሌላው ጋራ፣ አባትንና ወንድ ልጅን እርስ በእርስ አጋጫለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር፤ ያለ ሐዘኔታ፣ ያለ ምሕረትና ያለ ርኅራኄ አጠፋቸዋለሁ።’ ”
ቢጾሙም ጩኸታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ቢያቀርቡም አልቀበላቸውም፤ ነገር ግን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር አጠፋቸዋለሁ።”
የሰባቶቹ እናት ትዝለፈለፋለች፤ ትንፋሿም ይጠፋል፤ ገና ቀን ሳለ ፀሓይዋ ትጠልቃለች፤ እርሷም ታፍራለች፤ ትዋረዳለችም፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት፣ ለሰይፍ እዳርጋቸዋለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።
“ ‘በዚህ ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ዕቅድ አፈርሳለሁ፤ በጠላቶቻቸው ፊት ሕይወታቸውን በሚሹት እጅ በሰይፍ እንዲወድቁ አደርጋለሁ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘አንተንና ወዳጆችህ ሁሉ ለሽብር እዳርጋለሁ፤ የገዛ ዐይንህ እያየ በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። ይሁዳን ሁሉ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል፤ በሰይፍም ይገድላቸዋል።
የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፎ ይሰጣል፤ ፊት ለፊትም ያነጋግረዋል፤ በዐይኖቹም ያየዋል እንጂ ከባቢሎናውያን እጅ አያመልጥም።
አንተም በርግጥ ትያዛለህ፤ ዐልፈህም ለርሱ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም። የባቢሎንን ንጉሥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ፊት ለፊትም ያነጋግርሃል፤ ወደ ባቢሎንም ትሄዳለህ።
ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የባቢሎን ንጉሥ በርግጥ ይመጣል፤ ይህችን ምድር፣ በርሷም ላይ የሚኖሩትን ሰዎችንና እንስሳትን ያጠፋል በማለት የጻፍህበት ለምንድን ነው?” ብለህ ብራናውን አቃጥለሃል።
ከዚያም በኋላ ንጉሡ ሴዴቅያስ ላከበትና ወደ ቤተ መንግሥት አስመጣው፤ ለብቻውም ወስዶ፣ “ከእግዚአብሔር የመጣ ቃል አለህ?” በማለት ጠየቀው። ኤርምያስም፣ “አዎን አለ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፈህ ትሰጣለህ” አለው።
“እስራኤል አንበሶች ያሳደዱት፣ የተበተነ መንጋ ነው፤ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ፣ ቦጫጭቆ በላው፤ በኋላም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ ዐጥንቱን ቈረጣጠመው።”
“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እይ፤ ተመልከትም፤ በማን ላይ እንዲህ አድርገህ ታውቃለህ? በውኑ እናቶች ሕፃኖቻቸውን፣ ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆች ይብሉን? ካህኑና ነቢዩስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገደሉን?
“በበዓል ቀን ለግብዣ እንደምትጠራ፣ ሽብርን ከየአቅጣጫው በእኔ ላይ ጠራህ፤ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ማንም አላመለጠም ወይም አልተረፈም፤ የተንከባከብኋቸውንና ያሳደግኋቸውን፣ ጠላቴ አጠፋብኝ።”
በርኅራኄ ዐይን አልመለከትሽም፤ ምሕረት አላደርግልሽም፤ ስለ አካሄድሽና በመካከልሽ ስላለው ጸያፍ ተግባር፣ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ፤ በዚያ ጊዜ፣ የምቀሥፍ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።