ዘካርያስ 1:11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነርሱም “ምድርን ሁሉ ዞረን መረመርን፤ ምድሪቱ በመላ ሰላም ነች” ብለው ለመልአኩ ነገሩት። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ለነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፣ “በምድር ሁሉ ተመላለስን፤ መላዋ ምድርም ዐርፋ በሰላም ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ለነበረው ለጌታ መልአክ፥ “ምድርን አሰስናት፥ እነሆም፥ መላዋ ምድር በጸጥታ ዐርፋ ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረውን የእግዚአብሔርን መልአክ፦ በምድር ላይ ተመላለስን፥ እነሆም፥ ምድር ሁሉ ዝም ብላ ዐርፋ ተቀምጣለች ብለው መለሱለት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረውን የእግዚአብሔርን መልአክ፦ በምድር ላይ ተመላለስን፥ እነሆም፥ ምድር ሁሉ ዝም ብላ ዐርፋ ተቀምጣለች ብለው መለሱለት። |
እንደገናም እንዲህ አለኝ፦ “ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደ ሆነ ታውቃለህን? እኔ ወደ አንተ የመጣሁት በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን ልገልጥልህ ነው፤ አሁንም ተመልሼ የፋርስ መንግሥት አለቃ ከሆነው መንፈስ ጋር ጦርነት አደርጋለሁ፤ እኔ ከሄድኩ በኋላ የግሪክ መንግሥት አለቃ የሆነው መንፈስ ይመጣል፤ ይሁን እንጂ የእስራኤል ጠባቂ መልአክ ከሆነው ከሚካኤል በቀር እኔን የሚረዳ የለም።
ሰላም አግኝተው በጸጥታ በሚኖሩ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ እጅግ ተቈጥቼአለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሕዝቤን ከመቅጣት መለስ ባልኩበት ጊዜ እነዚያ የአሕዛብ መንግሥታት ሕዝቤን ከተጠበቀው በላይ አሠቃይተዋል።
የእግዚአብሔር መልአክ በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አየሁ። እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆመ፤ በስተኋላውም ቀይ፥ ሐመርና አምባላይ ፈረሶች ይከተሉት ነበር።
በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤
ሰዎች “ሁሉ ነገር ሰላምና የተረጋጋ ነው” ሲሉ እርጉዝ ሴትን ምጥ እንደሚይዛት ዐይነት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ በምንም ዐይነት አያመልጡም።
አሁን መከራን ለምትቀበሉትም ከእኛ ጋር ዕረፍትን ይሰጣችኋል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ ከኀያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚወርድበት ጊዜ ነው፤
ይህ ራእይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳያቸው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም መልአኩን ልኮ ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ይህን ራእይ ገለጠለት።