ማርቆስ 12:17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም በመልሱ ተደነቁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ኢየሱስም፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በርሱ እጅግ ተደነቁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ኢየሱስም፥ “የቄሣርን ለቄሣር፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በእርሱ ተደነቁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ኢየሱስም መልሶ “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ኢየሱስም መልሶ፦ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። |
የሠራዊት አምላክ ካህናቱን እንዲህ ይላቸዋል፦ “ልጅ አባቱን፥ አገልጋይም አሳዳሪ ጌታውን ያከብራል፤ እነሆ፥ እኔ አባታችሁ ከሆንኩ ለምን አታከብሩኝም? ጌታችሁም ከሆንኩ ለምን ክብር አትሰጡኝም? እናንተ የእኔን ስም ንቃችኋል፤ ነገር ግን ‘ስምህን የናቅነው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ።
እነርሱም፥ “የሮማው ንጉሠ ነገሥት ነው!” አሉት፤ እርሱም፥ “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ፤” አላቸው።
ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህን የሚያኽል ትልቅ እምነት ያለው አንድም ሰው በእስራኤል ስንኳ አላገኘሁም።
እነርሱም ገንዘቡን አመጡለት፤ እርሱም “በዚህ ገንዘብ ላይ ያለው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው፤” አሉት።
እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ፥ ሕያውና የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጋችሁ ሁለንተናችሁን እንድታቀርቡ በመሐሪው በእግዚአብሔር ስም እለምናችኋለሁ፤ ይህም ማቅረብ የሚገባችሁ ቅንነት ያለው እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልግሎት ነው።
እንግዲህ ለበላይ ባለሥልጣን ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ አድርጉ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ፤ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ።
እንዲሁም የሰውነታችሁን ክፍሎች የዐመፅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታስገዙ፤ ነገር ግን ከሞት ተነሥታችሁ ሕያዋን እንደ ሆናችሁ በማድረግ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች ሁሉ የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አስገዙ።