ማርቆስ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ወይን አትክልቱ ሠራተኞች ምሳሌ ( ማቴ. 21፥33-46 ፤ ሉቃ. 20፥9-19 ) 1 በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 2 በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ 3 ይዘውም ደበደቡት፤ ባዶውንም ሰደዱት። 4 ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ፤ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት፤ አዋርደውም ሰደዱት። 5 ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፤ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ፤ አንዳንዱንም ገደሉ። 6 የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ‘ልጄንስ ያፍሩታል፤’ ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ። 7 እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለው፤ ርስቱም ለኛ ይሆናል፤’ ተባባሉ። 8 ይዘውም ገደሉት፤ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት። 9 እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ያጠፋል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። 10-11 ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው።’ የሚለውን ይህን መጽሐፍ አላነበባችሁምን?” 12 ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ። ለቄሳር ግብር ስለ መክፈል ( ማቴ. 22፥15-22 ፤ ሉቃ. 20፥20-26 ) 13 በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። 14 መጥተውም “መምህር ሆይ! የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሳር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ?” አሉት። 15 እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ፤” አላቸው። 16 እነርሱም አመጡለት። “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” አላቸው፤ እነርሱም “የቄሳር ናት፤” አሉት። 17 ኢየሱስም መልሶ “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። ስለ ትንሣኤ ሙታን ( ማቴ. 22፥23-33 ፤ ሉቃ. 20፥27-40 ) 18 ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት 19 “መምህር ሆይ! ሙሴ “የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ፤’ ብሎ ጻፈልን። 20 ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ 21 ሁለተኛውም አገባት፤ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22 ሰባቱም አገቡአት፤ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 23 ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?” 24 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? 25 ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። 26 ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? 27 የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።” ከሁሉ የምትበልጥ ትእዛዝ ( ማቴ. 22፥34-40 ፤ ሉቃ. 10፥25-28 ) 28 ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ “ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት?” ብሎ ጠየቀው። 29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ 30 አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኀይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፤’ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 31 ሁለተኛይቱም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤’ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።” 32 ጻፊውም “መልካም ነው፤ መምህር ሆይ! ‘አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ የለም፤’ ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ 33 በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኀይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው፡” አለው። 34 ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ያቀረበው ጥያቄ ( ማቴ. 22፥41-46 ፤ ሉቃ. 20፥41-44 ) 35 ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ “ጻፎች ‘ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው፤’ እንዴት ይላሉ? 36 ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ‘ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።’ 37 ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። ከጻፎች ሥራ ስለ መጠበቅ ( ማቴ. 23፥1-36 ፤ ሉቃ. 20፥45-47 ) 38-39 ሲያስተምርም እንዲህ አለ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብዣም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 40 የመበለቶችን ቤት የሚበሉ፤ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” የመበለቲቱ ስጦታ ( ሉቃ. 21፥1-4 ) 41 ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ 42 አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። 43 ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ “እውነት እላችኋለሁ፤ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ 44 ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች፤” አላቸው። |