ኢሳይያስ 45:6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህንንም የማደርገው መላው ዓለም እኔ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቅ ዘንድ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ይኸውም ሰዎች ከፀሓይ መውጫ፣ እስከ መጥለቂያው፣ ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ ነው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ፥ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ይወቁ እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ፤ ከእኔም ሌላ አምላክ የለም። |
በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ምንም ጒዳት አይደርስም፤ ባሕር በውሃ እንደሚሞላ ምድርም እግዚአብሔርን በሚያውቁና በሚያከብሩ ሰዎች ትሞላለች።
“እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ተረድታችሁ ታውቁኝና ታምኑብኝ ዘንድ የመረጥኳችሁ አገልጋዮቼና ምስክሮቼ እናንተ ናችሁ። በእርግጥ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ከእዚህ በፊት አልነበረም፤ ወደ ፊትም አይኖርም።
የሠራዊት አምላክ፥ የእስራኤል ንጉሥና አዳኝ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም።
“አንቺ በልብሽ ‘እንደ እኔ ያለ ማንም የለም፤ ባልዋ እንደ ሞተባት ሴት ሆኜ አልኖርም፤ ወይም የልጅ ሞት አይደርስብኝም’ ብለሽ በመዝናናት የተቀመጥሽው ቅምጥሊቱ ሆይ! ይህን ስሚ፦
ጨቋኞችሽ የገዛ ሥጋቸውን እንዲበሉ አደርጋለሁ፤ በወይን ጠጅ እንደሚሰክሩ የገዛ ደማቸውን ጠጥተው እንዲሰክሩ አደርጋለሁ። ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽና ታዳጊሽ የእስራኤል ኀያል አምላክ መሆኔን የዓለም ሕዝብ ሁሉ ያውቃል።”
በዚህም ዐይነት ታላቅነቴንና ቅድስናዬን አሳያለሁ፤ በብዙ ሕዝቦችም ዘንድ ራሴን አሳውቃለሁ፤ ከዚያ በኋላ እነርሱ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”
ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ክብሬን በሕዝቦች መካከል እገልጣለሁ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ተግባራዊ ያደረግኹትን ፍርዴንና እነርሱን የቀጣሁበትን ኀይሌን ያያሉ።
ሕዝቤ ሆይ! እኔ በመካከላችሁ እንዳለሁ፥ አምላካችሁም እኔ ብቻ እንደ ሆንኩና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ኀፍረት አይደርስባቸውም።”
እነሆ፥ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዳር እስከ ዳር ለእኔ ክብር ይሰጣሉ፤ በየትኛውም ስፍራ ለእኔ ዕጣን እያጠኑ ንጹሕ መሥዋዕት ያቀርቡልኛል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ያከብሩኛል።