መክብብ 1:13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ታዲያ፥ በዚህ ዓለም የተደረጉትን ነገሮች ሁሉ በጥበብ መርምሬ ለማጥናት ወሰንኩ፤ ይህችን ከባድ ጭነት የሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር ሰጥቶአቸዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከሰማይ በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ ለማጥናትና ለመመርመር ራሴን አተጋሁ፤ አምላክ በሰዎች ላይ የጫነው እንዴት ያለ ከባድ ሸክም ነው! መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፥ ይደክሙባት ዘንድ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጣት ከባድ ጥረት ናት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ከሰማይም በታች ስለተደረገው ሁሉ በጥበብ ለመመርመርና ለመፈተን ልቤን አተጋሁ፤ እግዚአብሔር ይደክሙበት ዘንድ ክፉ ድካምን ለሰው ልጆች ሰጥትዋልና። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፥ እግዚአብሔር ይደክሙባት ዘንድ ይህችን ለሰው ልጆች የሰጠ ክፉ ጥረት ናት። |
ሰዎች ጨለማን በማስወገድ እስከ መሬቱ ጥልቀት ዘልቀው በመግባት ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ውስጥ በመግባት በድቅድቅ ጨለማው ውስጥ የማዕድን ድንጋይ ይፈልጋሉ።
የነፋስን አካሄድና የሰውም ሕይወት አፈጣጠር በእናቱ ማሕፀን እንዴት እንደሚጀመር እንደማታውቅ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እግዚአብሔር ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ማወቅ አትችልም።
በሕይወቱ ዘመን የሚሠራው ነገር ሁሉ ከሐዘንና ከትካዜ በቀር የሚያተርፍለት ምንም ዐይነት ጥቅም የለም፤ ሌሊት እንኳ አእምሮው ዕረፍት አያገኝም፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ነው።
እግዚአብሔር ደስ ለሚያሰኘው ሰው ብቻ ጥበብን፥ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ሰው ግን ድካምን ብቻ ያተርፍለታል፤ ስለዚህም እርሱ ያከማቸውን ሀብት ሁሉ ምንም ላልደከመበት እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኝ ለሌላ ሰው ትቶለት እንዲያልፍ ያደርገዋል፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ በመወሰን ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ ሠርቶታል፤ ዘለዓለማዊነትንም በሰው ልቡና አሳድሮአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሁሉ እስከ መጨረሻ ያውቅ ዘንድ ለሰው የተሰጠው ዕውቀት ሙሉ አይደለም።
ደግሞም ሰዎች የተመኙትን ለማግኘት ተግተው በመሥራት ምን ያኽል እንደሚደክሙ ተመለከትኩ፤ ይህንንም የሚያደርጉት በባልንጀሮቻቸው ላይ በመቅናት መሆኑን ተረዳሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።
እነሆ፥ ብቻውን የሚኖር አንድ ሰው አለ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ይሁን እንጂ ዘወትር በሥራ ከመድከም አይቦዝንም፤ ባገኘውም ሀብት በቃኝ ማለትን አላወቀም፤ “እርሱም የምደክመው ለማን ነው? ለራሴስ ደስታን የምነፍገው ለምንድን ነው?” ብሎ ራሱን ይጠይቃል፤ ይህ ሁሉ የባሰ ከንቱና የሥቃይ ሕይወት ነው።
ጥበብንና የነገሮችን ሁናቴ ለመረዳት፥ ለማጥናትና ለመመርመር አሰብኩ፤ ይህም ክፋት ሞኝነት መሆኑን፥ ሞኝነትም እብደት መሆኑን ወደማወቅ አደረሰኝ።
በዚህ ዓለም የሚካሄደውን ሁናቴ በጥሞና ስመለከት ይህን ሁሉ አስተዋልኩ፤ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ለመጒዳት ሥልጣን የሚኖረው ለምንድን ነው?