ሐዋርያት ሥራ 23:6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ጳውሎስ እዚያ ከነበሩት ሰዎች እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ዐውቆ “ወንድሞቼ ሆይ! እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ፤ እነሆ! አሁን በፍርድ ፊት የቀረብኩት በተሰጠው ተስፋና በሙታን ትንሣኤ ምክንያት ነው” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ በሸንጎው መካከል ተናገረ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ጳውሎስም ሕዝቡ፣ ከፊሎቹ ሰዱቃውያን፣ ከፊሎቹ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ፣ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ሲል በሸንጎው ፊት ጮኸ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጳውሎስ ግን እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ “ወንድሞች ሆይ! እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል፤” ብሎ በሸንጎው ጮኸ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ጳውሎስም እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹም ፈሪሳውያን እንደ ሆኑ ዐውቆ፥ “እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊ ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣትም ይፈረድብኛል” ብሎ በአደባባይ ጮኸ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ፦ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ። |
ነገር ግን፥ ዮሐንስ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ለመጠመቅ ወደ እርሱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእባብ ልጆች! ከሚመጣው ቊጣ እንድታመልጡ ማን አስጠነቀቃችሁ?
“እኔ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ ያደግኹት ግን በዚህች በኢየሩሳሌም ከተማ ነው። አስተማሪዬም ገማልያል ነበር፤ የአባቶችን ሕግ ጠንቅቄ የተማርኩና ልክ ዛሬ እናንተ እንደምታደርጉት እግዚአብሔርን በመንፈሳዊ ቅናት የማገለግል ነበርኩ።
በማግስቱ አዛዡ፥ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበት ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ፈለገ፤ ስለዚህ የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም ከእስራቱ ፈቶ ወሰደና በፊታቸው አቀረበው።
ይህም እውነት መሆኑን የካህናት አለቃውና የሽማግሌዎች ሸንጎ በሙሉ ይመሰክሩልኛል። እንዲያውም በደማስቆ ያሉትን እነዚህን ሰዎች አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣትና ለማስቀጣት የሚያስችለኝን በደማስቆ ወደሚገኙት ወገኖቻቸው የጻፉትን ደብዳቤ የተቀበልኩት ከእነርሱ ነው።
ጳውሎስም ሸንጎውን ትኲር ብሎ ተመለከተና “ወንድሞቼ ሆይ! እስከ ዛሬ ድረስ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የኖርኩት በመልካም ኅሊና ነው” አለ።
ስለዚህ እናንተ ከሸንጎው ጋር ተስማምታችሁ በጥብቅ የምትመረምሩት ነገር እንዳለ በማስመሰል ጳውሎስን እንዲያመጡላችሁ አዛዡን ጠይቁት፤ እኛም እዚህ ከመድረሱ በፊት ልንገድለው ተዘጋጅተናል።”
እርግጥ በመካከላቸው ቆሜ ‘የሙታን ትንሣኤ አለ በማለቴ ዛሬ ለፍርድ በፊታችሁ ቀርቤአለሁ’ ብዬ ከፍ ባለ ድምፅ ተናግሬአለሁ፤ ከዚህ በቀር ሌላ ያደረግኹት ነገር የለም።”
አሁንም ያስጠራኋችሁ እንዳያችሁና ይህንንም እንድነግራችሁ ነው፤ እኔ በዚህ በሰንሰለት የታሰርኩት ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”
እኔ በተወለድኩ በስምንተኛው ቀን ተገርዤአለሁ፤ በትውልዴም ከብንያም ነገድ የሆንኩ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከዚህም የተነሣ ጥርት ያልኩ ዕብራዊ ነኝ። የአይሁድን ሕግ ስለ መጠበቅም ቢሆን ፈሪሳዊ ነበር።
የእውነት ቃል የሆነው ወንጌል በመጀመሪያ ወደ እናንተ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ያለውን ተስፋ ሰምታችኋል፤ ስለዚህ እምነታችሁና ፍቅራችሁ የተመሠረተው በሰማይ ተዘጋጅቶ በሚቈያችሁ በዚህ ተስፋ ላይ ነው።