ሐዋርያት ሥራ 17:28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ‘ሕይወት የምናገኘውና የምንንቀሳቀሰው፥ የምንኖረውም በእርሱ ነው፤’ ይህም የእናንተ ባለ ቅኔዎች ‘እኛ ሁላችን የእርሱ ልጆች ነን’ እንዳሉት ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በርሱ ነውና። ከራሳችሁ ባለቅኔዎችም አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ ‘እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን።’ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ ‘እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና፤’ ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን፤ እንኖርማለን። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እኛ በእርሱ ሕይወትን እናገኛለን፤ በእርሱም እንንቀሳቀሳለን፤ በእርሱም ጸንተን እንኖራለን፤ ከመካከላችሁም፦ ‘እኛ ዘመዶቹ ነን’ የሚሉ ፈላስፎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። |
ስለዚህም ንጉሥ ሴዴቅያስ “እኔ አልገድልህም፤ ለሚገድሉህም ሰዎች አሳልፌ ላልሰጥህ ሕይወትን በሰጠን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ!” በማለት በምሥጢር ቃል ገባልኝ።
ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ ከቤተ መቅደሱ ተዘርፈው የመጡትን የወርቅ ዕቃዎች አስመጥተህ አንተና መኳንንቶችህ፥ ሚስቶችህና ቁባቶችህ የወይን ጠጅ መጠጫ አደረጋችኋቸው፤ ከጠጣችሁም በኋላ ማየት ወይም መስማት የማይችሉትንና ምንም ነገር የማያውቁትን ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገናችሁ፤ መግደል ወይም ማዳን የሚችለውንና አካሄድህን የሚቈጣጠረውን ሕያው አምላክ ግን አላከበርከውም።
አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፤ ለእርሱም ታዛዥ ሁን፤ በእርሱም እመን፤ ይህም ለአንተ ሕይወት ከመሆኑም በላይ ለቀድሞ አባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ቃል በገባላቸው መሠረት ገብተህ በምትኖርባት ምድር ለረጅም ዘመን ትኖራለህ።”
እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው፤ እርሱ በባሕርዩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ትክክል ነው። በኀያል ቃሉ ዓለምን ሁሉ ደግፎ ይዞአል፤ ሰዎችንም ከኃጢአት ካነጻ በኋላ በሰማይ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል።
ከዚህም በቀር እኛ ሁላችን የሚቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ፥ በሕይወት ለመኖር ለመንፈሳዊ አባታችን በይበልጥ መታዘዝ እንዴት አይገባንም!
ሰዎችን ቅዱሳን የሚያደርጋቸውና በእርሱ ቅዱሳን የሆኑትም ሰዎች የአንድ አባት ልጆች ናቸው፤ በዚህ ምክንያት ኢየሱስ እነርሱን “ወንድሞቼ” ብሎ ለመጥራት አያፍርም።
ማንም ሰው በአንተ ላይ አደጋ ጥሎ ሊገድልህ ቢፈልግ አንድ ሰው ውድ የሆነ ሀብቱን እንደሚጠብቅ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን በሰላም ይጠብቅሃል፤ ስለ ጠላቶችህም የሆነ እንደ ሆነ አንድ ሰው ድንጋዩን ከወንጭፍ እንደሚያስፈነጥር እግዚአብሔር ራሱ አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል።