ዘዳግም 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምወደ እግዚአብሔር በመመለስ የሚገኝ በረከት 1 “እኔ ዛሬ በፊትህ በበረከትና በመርገም መካከል ምርጫን ሰጥቼሃለሁ፤ እግዚአብሔር በሕዝቦች መካከል በበተነህ ቦታ ሆነህ ብታስታውሰው 2 አንተ ከዘሮችህ ጋር ወደ እግዚአብሔር ብትመለስና ዛሬ እኔ ለምሰጥህ ለእግዚአብሔር ሕጎች ከልብ ታዛዥ ሆነህ ብትገኝ፥ 3 አምላክህ እግዚአብሔር ምሕረት ያደርግልሃል፤ በአሕዛብ መካከል አንተን ከበታተነበት ስፍራ ሁሉ መልሶ በማምጣት እንደገና ያበለጽግሃል። 4 እስከ ምድር ዳርቻ ተበታትነህ የምትኖር ብትሆን እንኳ አምላክህ እግዚአብሔር በአንድነት በመሰብሰብ መልሶ ያመጣሃል፤ 5 በዚህም ዐይነት የቀድሞ አባቶችህ የነበሩበትን ምድር እንደገና ትወርሳለህ፤ እርሱም ከቀድሞ አባቶችህ ይበልጥ ባለጸጋና ቊጥርህ የበዛ እንድትሆን ያደርጋል። 6 አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለልጆችህ ታዛዥ ልብ ይሰጣል፤ ስለዚህም እርሱን በፍጹም ልብህ ትወደዋለህ፤ በዚያችም ምድር በሕይወት ትኖራለህ። 7 እነዚህንም መርገሞች ሁሉ አንተን በሚጠሉህና በሚጨቊኑህ ጠላቶችህ ላይ ይመልስባቸዋል፤ 8 አንተም እንደገና ለእርሱ ታዛዥ ትሆናለህ፤ ዛሬ እኔ የምሰጥህንም የእርሱን ትእዛዞች ትጠብቃለህ፤ 9 በምትሠራው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያበለጽግሃል፤ ልጆችህን፤ እንስሶችህንና የምድርህን ሰብልና ፍሬ ያበዛልሃል፤ እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶችህን በማበልጸግ ደስ ይለው እንደ ነበር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋል። 10 ይህንንም የሚያደርገው በዚህ የሕግ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉትን ትእዛዞችና ሕጎች በመጠበቅ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር የተመለስክ እንደ ሆነ ነው። በሕይወትና በሞት መካከል የሚደረግ ምርጫ 11 “ዛሬ እኔ የምሰጥህ ትእዛዝ በጣም ከባድ ወይም ከአንተ የራቀ አይደለም፤ 12 ‘እርሱን ሰምተን እንታዘዘው ዘንድ ማን ወጥቶ ያመጣልናል’ ብለህ እንዳትጠይቅ፥ ይህ ሕግ የሚገኘው በሰማይ አይደለም። 13 ‘እርሱን ሰምተን እንታዘዘው ዘንድ ከባሕር ማዶ ተሻግሮ ማን ሊያመጣልን ይችላል?’ ብለህ እንዳትጠይቅ፥ እርሱ የሚገኘው ከባሕር ማዶ አይደለም። 14 ቃሉ ለእናንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ትጠብቀውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ይገኛል። 15 “ዛሬ እኔ ሕይወትንና መልካምነትን ወይም ሞትንና ክፋትን እንድትመርጥ ሰጥቼሃለሁ፤ 16 ዛሬ እኔ ለማዝህ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትእዛዞች ታዛዥ ብትሆን፥ በሕጉ ብትመራ፥ ትእዛዞቹን፥ ሕጎቹንና ሥርዓቱን ብትጠብቅ በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ አምላክህ እግዚአብሔርም በምትገባበት ምድር ይባርክሃል። 17 ነገር ግን ልብህን ከእግዚአብሔር አርቀህ ቃሉን የማትሰማ ብትሆን፥ ለሌሎችም አማልክት ልትሰግድላቸውና ልታመልካቸው ብትባክን፥ 18 እንደምትደመሰስ እነሆ፥ ዛሬ አስጠነቅቅሃለሁ። ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሳት ምድር ለረጅም ዘመን አትኖርም። 19 እነሆ፥ እኔ በሕይወትና በሞት መካከል፥ በእግዚአብሔር በረከትና መርገም መካከል ምርጫ እሰጣችኋለሁ፤ በምታደርጉትም ምርጫ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ ምስክር አድርጌ እጠራለሁ፤ ስለዚህም እናንተና ዘሮቻችሁ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጡ። 20 አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፤ ለእርሱም ታዛዥ ሁን፤ በእርሱም እመን፤ ይህም ለአንተ ሕይወት ከመሆኑም በላይ ለቀድሞ አባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ቃል በገባላቸው መሠረት ገብተህ በምትኖርባት ምድር ለረጅም ዘመን ትኖራለህ።” |