2 ዜና መዋዕል 26:5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም መንፈሳዊ አማካሪው ዘካርያስ በሕይወት እስከ ነበረበት ዘመን ድረስ ዖዝያ እግዚአብሔርን በታማኝነት ያገለግል ነበር፤ እግዚአብሔርም ባረከው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታንም መፍራት ባስተማረው ዘካርያስ በእርሱም ዘመን ጌታን ለመፈለግ ልቡን አቀና፤ ጌታንም በፈለገ ጊዜ ጌታ ነገሩን አከናወነለት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርንም መፍራት ባስተማረ በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ፤ በዘመኑም እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርም ነገሩን አከናወነለት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርንም መፍራት ባስተማረ በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ፤ እግዚአብሔርንም በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር ነገሩን አከናወነለት። |
ዳዊት ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለእርሱ ቤተ መቅደስ ትሠራለት ዘንድ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ሁሉን ነገር ያከናውንልህ፤
እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጎችንና ሥርዓቶችን ሁሉ ብትፈጽም፥ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ በርታ፤ ቈራጥ ሁን፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቊረጥ።
ዐዛርያስም ከንጉሥ አሳ ጋር ለመገናኘት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ አሳ ሆይ! አድምጠኝ! እናንተም የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ስሙኝ! እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር እስከ ሆናችሁ ድረስ እርሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ከፈለጋችሁትም ታገኙታላችሁ፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል፤
“አንተ በዚህ በምታደርገው ጦርነት የእስራኤል ወታደሮች ድጋፍ ይሆኑኛል ብለህ ታስብ ይሆናል፤ ነገር ግን አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ እንድትሆን የሚያደርግህ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እነሆ አሁንም እርሱ በጠላቶችህ ድል እንድትሆን ያደርግሃል።”
ሕዝቅያስ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ሲሆነው ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱ አቢያ ተብላ የምትጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበረች።
በላይ በኩል ያለውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ ውሃውን ወደ ምዕራብ፥ ወደ ዳዊት ከተማ፥ በቦይ እንዲወርድ ያደረገ ራሱ ሕዝቅያስ ነው፤ ይህ ሕዝቅያስ ሊሠራ ባቀደው ነገር ሁሉ የተሳካለት ሰው ነበር፤
እርሱም፦ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፥ ቅጠሏም እንደማይረግፍ፥ በፈሳሽ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሥራ ሁሉ ይሳካለታል።
እግዚአብሔርም ለእነዚህ ለአራት ወጣቶች በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው።
የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ሌላ ራእይ ተገለጠለት፤ በራእዩም የተነገረው ቃል እውነት ነው፤ ነገር ግን ለማስተዋል እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ትርጒሙ በራእይ ተገለጠለት።
አንተ ግን የተሰወረውን ነገር የመተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር ሁሉ የመፍታት ችሎታ እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጒሙን ብትነግረኝ፥ ሐምራዊ መጐናጸፊያ እንድትለብስ፤ የወርቅ ኒሻን በአንገትህ እንድታደርግና በመንግሥቴም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕርግ እንድትይዝ አደርጋለሁ።”
እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! እናንተን ምን ላድርጋችሁ? እናንተ ለእኔ ያላችሁ ፍቅር እንደ ማለዳ ጉምና እንደ ጠዋት ጤዛ ፈጥኖ ይጠፋል።
አንተ ብቻ አይዞህ፤ በርታ፤ አገልጋዬ ሙሴ ለሰጠህም ሕግ ሁሉ እውነተኛ ታዛዥ ሁን፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ ማናቸውም ነገር እንዲሳካልህ ከዚህ ሕግ ከቶ ዝንፍ አትበል፤
ይህን የሕግ መጽሐፍ ምን ጊዜም ከማንበብ አትቈጠብ፤ በእርሱ የተጻፈውን ሁሉ መፈጸም ትችል ዘንድ እርሱን ሌሊትና ቀን አሰላስለው፤ ይህንን ብታደርግ፥ ሁሉ ነገር በተቃና ሁኔታ ይሳካልሃል።
በኢያሱ ዘመንና በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ታላቅ ሥራ ባዩት ሽማግሌዎች የሕይወት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ።